ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

በአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች 2ተኛ ዓመታዊ ጉባኤ በሙያዊ ስነምግባር ላይ ያተኮረ ስልጠና እና ውይይት ተካሄደ

በአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች 2ተኛ ዓመታዊ ጉባኤ በሙያዊ ስነምግባር ላይ ያተኮረ ስልጠና እና ውይይት ተካሄደ

ባህር ዳር፣ መስከረም 20/2019 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በልዩ ትኩረት ከሚሰራባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የዳኞችን የሞያ ሥነ-ምግባር ማሳደግ ነው።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፣ "የዳኝነት ተደራሽነትን ማስፋት፣ አገልግሎትን ማላቅ" በሚል መሪ ቃል ለሁለተኛ ጊዜ በማካሄድ ላይ በሚገኘው የዳኞች ጉባኤ የመጀመሪያ ቀን ውሎ የሥነ ምግባር ግንባታ ላይ ሥልጠና ሰጧል።

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚታዩ የሥነ-ምግባር ችግሮችን ለመፍታት በማለም በሁሉም ፍርድ ቤቶች የሚገኙ ዳኞችን ያሳተፈ የሥነ-ምግባር ጥናት ያካሄደ መሆኑ የሚታወስ ነው።

በጥናቱ የተገኙ ግኝቶችንም በሕግና ፍትሕ ጉዳዮች የግል አማካሪ የሆኑት አቶ ማንደፍሮት በላይ "የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የሥነ- ምግባር ሁኔታ፣ በዳኞች እይታ" በሚል እርስ ለጉባእው ተሳታፊ ዳኞች አቅርበዋቸዋል ።

ለጉባኤው ተሳታፊዎች፣ በክልሉ ውስጥ በጉልሕ የሚታዩ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ እና የሥነ-ምግባር ችግሮች እና መንስኤዎች፣ የሥነ-ምግባር ሥልጠና መስጠት አስፈላጊነት፣ የሥነ-ምግባር ስልጠና አሰጣጥ እና መሠል ጉዳዮችን ለመለየት በማሰብ የተደረገው ጥናት በዝርዝር ቀርቧል።

የቀረበውን ጥናት ተከትሎ፣ በጉባኤው የከሰዓት ውሎ፣ ትኩረቱን ሙያዊ ሥነ-ምግባር ላይ ያደረገ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።

የፓናል ውይይቱ፣ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት መንገሻ አየን(ዶ/ር) በሞደሬተርነት፣ የቀድሞው ዳኛ እና ጠበቃ አቶ ባዩ በዛብህ፣ የአመልድ ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አለማየሁ ዋሴ(ዶ/ር) ፣ የወንጀል ፍትሕና የፖለቲካ ሶሲዮሎጅ መምሕርና ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ፔቶሮ ቶጂ ከአሜሪካ በቀጥታ፣ እንዲሁም የጋምቢ ማስተማሪያ ሆስፒታል ባለቤትና ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ገበያው ጥሩነህ በፓናሊስትነት የተሳተፉበት ነበር።

በፓናል ውይይቱ፣ ሞያዊነት እና የሞያ ሥነ ምግባርን በተመለከተ ዝርዝር ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ ሞያውን ጠንቅቆ ማወቅ ብቻ ሳይሆን ሞያውን መሸከም የሚችል ሥነ ምግባር እና ትጋት አስፈላጊ መሆኑ ተነስቷል።

የዳኝነት ሙያ በመሠረታዊነት እውነትን ፍለጋ በመሆኑ ትጋት እና ሀቀኝነት ወይም ታማኝነትን የሚጠይቅ መሆኑ በውይይቱ ተነስቷል።

ታማኝነት ሲባልም ተከታታይ እና ወጥነት ያለው ባህሪ በማሳየት የሚገለጽ እና የማንነት መገለጫ ሊሆን የሚገባው መሆኑ ነው የተጠቆመው።

ዳኞች በሰው ሕይወት እና መብት ላይ እንዲወስኑ ስልጣን ያላቸው በመሆኑ ያላቸው የሞያ ሥነ ምግባርም በዛው ልክ ከፍ ባለ ሚዛን የሚታይ በመሆኑ ሙያዊ ሥነምግባርን የተላበሱ መሆን እንደሚገባቸው ተነስቷል።

ዳኞች በታማኝነት በማገልገል ብሎም በሚሰሩት ሥራ ከህሊና ወቀሳ ነጻ መሆናቸውን እርግጠኛ በመሆን ሞያቸውን ማክበር እና ማስከበር የሚገባቸው መሆኑም ነው የተመላከተው።

በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የካበተ የትምሕርት፣ የልምድ እና የሕይወት ተሞክሮ ያላቸው የውይይቱ ተሳታፊዎች፣ ባለሙያዊነት፣ ታማኝነት፣ ሙያዊ ብቃት፣ እውቀትን ለሕዝብ አገልግሎት ማዋል፣ ፍትሕ እና ርትዕ ላይ በሰፊው በመወያየት ልምድና ተሞክሯቸውን ለተሳታፊዎቹ አካፍለዋል።

በቀረቡ ውይይቶች መነሻነት ተሳታፊዎች ጥያቄና አስተያየት የሰጡ ሲሆን፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣

በተነሱት ነጥቦች ላይ ምላሽና ማጠቃለያ ሰጠዋል።

የዳኝነት ሙያ በባሕሪው የሚጠይቀው ከፍ ያለ ሙያዊ ስነምግባር አለ ያሉት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ ሕገመንግስታዊ እና ሕዝባዊ ሃላፊነት የተሰጣቸው ዳኞች ይህንን አክብረው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሙያዊ ስነምግባርን ተከትሎ መስራት መቼ የሚል ጥያቄ የለውም ያሉት ክቡር ፕሬዝደንቱ ፣ በማንኛውም ጊዜ እና ሰዓት ሙያዊ ስነምግባርን ተከትሎ መስራት ያስፈልጋልም ብለዋል።

የክልሉ ፍርድ ቤት ዳኞች ሙያቸውን አክብረው እና ለሙያዊ ስነምግባር ተገዥ በመሆን የተጣለባቸውን ሃላፊነት በብቃት እየተወጡ መሆናቸውን የጠቀሱት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው ፣ ዳኝነት የሁሉም መጠሪያ በመሆኑ ጥቂት ዳኞች በሚፈጽሙት ጥፋት ሁሉም ዳኞች ሊወቀሱ ስለማይገባ ይህንን የምንከታተልበት ሥርዓት ጠንካራ መሆን አለበት ብለው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *