ባሕር ዳር፣ ሐምሌ 10 /2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትና የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በክልሉ ፍርድ ቤቶች የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል፣ በተቋማዊ አቅም ግንባታ፣ በጥናትና ምርምር፣ በነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት፣ በሰው ኃይል ልማትና በሌሎች የፍትሕ ዘርፍ የለውጥ ሥራዎች በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል።
የመግባቢያ ሰነዱን የፈረሙት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው እና የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሳይህ ካሳው (ዶ/ር) ናቸው።
በፊርማ ሥነ-ስርዓቱ ወቅት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው እንደገለጹት፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የጀመራቸውን ሰፊ የዳኝነት ሪፎርምና የተቋማዊ ለውጥ ሥራዎች ቀጣይነት ለማረጋገጥ የተቋሙን፣ የአመራሩንና የባለሙያዎችን አቅም በተከታታይ መገንባት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በሕግ ትምህርት፣ በአቅም ግንባታ፣ በነፃ የሕግ ድጋፍ እና በማህበረሰብ አገልግሎት ያለው ልምድ ለፍርድ ቤቱ የለውጥ ጉዞ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
ክቡር ፕሬዝዳንቱ አክለውም፣ ስምምነቱ በወረቀት ላይ ብቻ የሚቀር ሳይሆን በዝርዝር የድርጊት መርሃ ግብር ታግዞ በተግባር እንዲተገበር፣ በዜጎች ሕይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጡ ሥራዎች በጋራ እንደሚከናወኑ እምነታቸውን ገልጸዋል።
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሳይህ ካሳው (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ዩኒቨርሲቲያቸው 58 የመጀመሪያ ዲግሪ እና 56 የሚጠጉ የድህረ ምረቃ ፕሮግራሞችን በ10 ኮሌጆችና ትምህርት ቤቶች እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፣ በተለይ የሕግ ትምህርት ቤቱ ለሀገሪቱ የፍትሕ ሥርዓት ብቁ ባለሙያዎችን በማፍራት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል።
ዶ/ር ሳይህ እንዳሉት፣ ዩኒቨርሲቲው ከፍርድ ቤቶችና ከሌሎች የፍትሕ ተቋማት ጋር በአቅም ግንባታ፣ በሥራ ላይ ስልጠና፣ በነፃ የሕግ አገልግሎት፣ በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት ዙሪያ ከዚህ ቀደምም በቅንጅት እየሰራ የነበረ ሲሆን፣ አዲሱ ስምምነት እነዚህን ጅምሮች በተቋማዊ መልኩ በማጠናከር ወደ ተጨባጭ ውጤት ለመቀየር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የጋራ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ከአጋር ድርጅቶችና ከፈንድ ሰጪ ተቋማት ድጋፍ በማግኘት በፍትሕ ዘርፉ ዘላቂ ለውጥ የሚያመጡ ሥራዎችን በጋራ ለማሳካት እንደሚሰሩ አስረድተዋል።
የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ በአቅም ግንባታ፣ በጥናትና ምርምር፣ በዕውቀት አስተዳደር፣ በነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት፣ በሰው ኃይል ልማት እና በሌሎች የጋራ የፍትሕ ልማት መርሃ ግብሮች ላይ የሁለቱን ተቋማት ትብብር በማጠናከር ለዘመናዊ፣ ቀልጣፋና ተደራሽ የፍትሕ አገልግሎት መስፋፋት ጉልህ አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።





