ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አጋርና ባለድርሻ አካላት በ ክልሉ ፍርድ ቤቶች የ2018 በጀት ዓመት እና የሦስት ዓመት የትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈጻጸም ላይ ተወያዩ

የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አጋርና ባለድርሻ አካላት በ ክልሉ ፍርድ ቤቶች የ2018 በጀት ዓመት እና የሦስት ዓመት የትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈጻጸም ላይ ተወያዩ

ባሕርዳር፣ ሐምሌ 09/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የ2018 በጀት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ እና ከ2016 እስከ 2018 ዓ.ም የተተገበረውን የሦስት ዓመት የትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈጻጸም ከአጋርና ባለድርሻ አካላት ጋር የሚገመግም የውይይት መድረክ አካሂዷል።

በመድረኩ በዲጂታላይዜሽን፣ በዳኝነት ጥራትና ነፃነት፣ በሰው ሀብት ልማት፣ በዳኝነት ተደራሽነት ማሻሻያ፣ የትብብር ሥራዎችና ሌሎች 11 የትራንስፎርሜሽን ፕሮጀክቶች የተከናወኑ ስራዎች ሪፖርት ለውይይት ቀርቧል።

በሪፖርቱም፣ በ2018 በጀት ዓመት የመዝገብ አፈጻጸም በጠቅላይ ፍርድ ቤት 89.52 በመቶ፣ በከፍተኛ ፍርድ ቤት 86.09 በመቶ እና በወረዳ ፍርድ ቤቶች 95.58 በመቶ መድረሱ ተገልጿል።

በዲጂታላይዜሽን ዘርፍ 2,564 መዛግብት በስማርት ችሎት እና 13,706 መዛግብት በኢ-ፋይሊንግ ሲስተም የተስተናገዱ ሲሆን፣ ለባለጉዳዮች ከ51.2 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማስቀረት መቻሉ ተገልጿል። እንዲሁም 6152 የጥሪ ማዕከል በሙሉ አቅሙ አገልግሎት መስጠት በጀመረበት በአጭር ጊዜ ውስጥ 2,966 ባለጉዳዮችን ማስተናገዱ ተገልጿል።

በባሕል ፍርድ ቤቶች በኩልም 15 የባሕል ፍርድ ቤቶች እውቅና ተሰጥቷቸው ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን፣ 7,318 ዳኞች ተመርጠው 736 የባሕል ፍርድ ቤት ማዕከላት መቋቋማቸው ተጠቅሷል።

በሁለት ወራት ውስጥ 1,048 መዛግብት እልባት በማግኘታቸው ለባለጉዳዮች 29.9 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ወጪ መቆጠቡም ተጠቁሟል።

የክልሉ ፍርድ ቤቶች የ 2018 በጀት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድና የሶስት ዓመቱ የትራንስፎርሜሽን ትግበራ በዝርዝር ለተሳታፊዎች የቀረበ ሲሆን፣ ተሳታፊዎችም በቀረበው ሪፖርት ላይ ሀሳብና አስተያይታቸውን ሰጠዋል።

የክልሉ ፍርድ ቤቶች የጀመሩት የለውጥ ስራ አርአያነት ያለው መሆኑን የጠቀሱት ተሳታፊዎቹ፣ ይሄንን ማሳካት የሚቻለው በጠንካራ አመራር እና ፈጻሚ በመሆኑ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝደንት ያላቸውን አድናቆት ገልጸው፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተከናወኑ ስራዎች በተሞክሮነት የሚወሱዱ ናቸው ብለዋል።

ተሳታፊዎቹ፣ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎችን ለማስቀጠል፣ ስር ፍርድ ቤቶች ድረስ ተደራሽ ለማድረግ እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ያሏቸውን ጥያቄዎች ያነሱ ሲሆን፣ ለተነሱት ጥያቄዎችም አጋርና ባለድርሻ አካላትን ያወያዩት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው ምላሽና ማብራሪያ ሰጠዋል።

ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው በውይይቱ ማጠቃለያ ንግግራቸው፣ በዳኞች አቅም ግንባታ፣ ሙያዊ ሥነ ምግባርን ማጠናከር እና ሙስና መከላከል፣ በባሕል ፍርድ ቤቶች ማስፋፊያ ላይ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ገልጸው፣ የተጀመሩ የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች ፈጣን፣ ጥራት ያለውና ተጠያቂ የፍትሕ አገልግሎት ለመስጠት ወሳኝ በመሆናቸው ይበልጥ ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *