ባሕር ዳር፣ ሐምሌ 09/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ2018 በጀት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ አፈጻጸምና ከ2016 እስከ 2018 ዓ.ም በተተገበረው የሦስት ዓመት የዳኝነት ትራንስፎርሜሽን ሥራ ከአጋርና ባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ ፍትሕና የሕግ የበላይነት ለአንድ ሀገር የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ እድገትና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረታዊ መሆናቸውን ገልጸው፣ ፍርድ ቤቶችም ሕግንና ማስረጃን መሠረት በማድረግ የዜጎችን መብት በመጠበቅ የሀገር ልማትና መረጋጋት ውስጥ የማይተካ ሚና እንዳላቸው ጠቁመዋል።
ክቡር ፕሬዝዳንቱ እንደገለጹት፣ ፍርድ ቤቱ በሀገር ደረጃ የተዘጋጀውን የዳኝነትና የፍትሕ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከክልሉ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማጣጣም የራሱን የሦስት ዓመት የለውጥ ዕቅድ አዘጋጅቶ በመተግበር በብዙ ዘርፎች ተጨባጭ ውጤቶችን አስመዝግቧል።
በተለይም የዳኞች፣ የፍርድ ቤት አመራሮችና ሠራተኞች አቅም ግንባታ፣ የሕግና ፍትሕ ኢንስቲትዩትን እንደገና በማደራጀት ወደ ሥራ ማስገባት፣ የአሠራር ሥርዓቶችን ማሻሻል፣ ቴክኖሎጂን በስፋት መጠቀም፣ የዳኝነት አገልግሎትን ተደራሽ፣ ቀልጣፋና ግልጽ ማድረግ እንዲሁም የተገልጋዮችን እርካታ ማሳደግ በዋና ዋናነት የተመዘገቡ ስኬቶች መሆናቸውን አስረድተዋል።
በክልሉ የባህል ፍርድ ቤቶች መቋቋማቸው ፍትሕን ለማስፋት ብቻ ሳይሆን ዘላቂ ሰላምንና ማኅበራዊ እርቅን ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቅሰው፣ በንግድና ኢንቨስትመንት ጉዳዮች ላይ የግልግል ዳኝነትን ለማጠናከር እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችም ለኢኮኖሚ እድገት ጉልህ ድርሻ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።
በ2018 በጀት ዓመት የመዝገብ ማጥራት፣ ጉዳዮችን በወቅቱ ለማጠናቀቅ፣ የፍርድ ጥራትን ለማሳደግና በሌሎች የአፈጻጸም መመዘኛዎች ከቀደሙት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ መሻሻል መመዝጠቡንም ክቡር ፕሬዝደንቱ ጨምረው ተናግረዋል ።
ለተገኘው ውጤት አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሁሉም ደረጃ ዳኞች፣ የፍርድ ቤት አመራሮች፣ ሠራተኞች፣ የፍትሕ ተቋማት፣ አጋር ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት ምስጋናቸውን ያቀረቡት ክቡር አቶ አለምአንተ፣ በቀጣይም የሕብረተሰቡን የፍትሕ ፍላጎት በተሻለ ሁኔታ ለማሟላት የበለጠ ትብብርና የጋራ ስራ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። በክልሉ ፍርድ ቤቶች የ2018 በጀት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ እና በሶስት ዓመቱ የትራንስፎርሜሽን ትግበራ አፈጻጸም ውይይት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን አመራሮች እና ዳኞች ጨምሮ፣ የክፍተኛ ፍርድ ቤቶች ፕሬዝደንቶች፣ የተለያዩ ቢሮዎች ሀላፊዎች፣ ከተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተወጣጡ የሕግ ምሁራን፣ ጠበቆች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች እና ሌሎች አጋርና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።







