ባሕር ዳር፣ ሰኔ 27/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በክልሉ የዳኝነትና የፍትሕ ሥርዓትን ለማዘመን፣ ተደራሽና ውጤታማ ለማድረግ በተለያዩ የትብብር መስኮች በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል።
በስምምነቱ ፊርማ ሥነ-ሥርዓት ወቅትም የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በትምህርት፣ በምርምር፣ በማሕበረሰብ አገልግሎት እና በሌሎች የአጋርነት ሥራዎች ያስመዘገበው ስኬት ከፍተኛ በመሆኑ ከተቋሙ ጋር የሚደረገው ትብብር የክልሉን የፍትሕ ሥርዓት ለማሻሻል ወሳኝ እንደሚሆን ገልጸዋል።
ክቡር ፕሬዝዳንቱ፣ ፍርድ ቤቱ ፍትሕን ተደራሽ፣ ፈጣንና ዘመናዊ ለማድረግ ሰፊ የሪፎርም ሥራዎችን እያከናወነ ሲሆን፣ በዚህም የአማራጭ የሙግት መፍቻ ሥርዓቶችን ማጠናከር፣ የባህል ፍርድ ቤቶችን ማስፋፋት፣ የሕግ ድጋፍ አገልግሎትን ማሻሻል፣ የጠበቆችን አቅም መገንባት፣ የፍርድ ቤት አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ ማድረግና የሰው ኃይል ልማትን ማጠናከር ዋና ትኩረቶች መሆናቸውን አስረድተዋል።
የተጀመሩ ሥራዎችን በተሻለ ውጤት ለማሳካት ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር በአቅም ግንባታ፣ በአጫጭርና ረጅም ጊዜ ስልጠናዎች፣ በሀገር በቀል የፍትሕ ሥርዓቶች ማጠናከር፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂዎች ልማት፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም አለም አቀፍ ኮንፈረንሶችንና የጋራ መድረኮች በማካሄድ በስፋት እንደሚሰራ አመልክተዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ዩኒቨርሲቲው ከ350 በላይ የትምህርት መርሃ ግብሮች እንዳሉት ጠቅሰው፣ በተለይም የሕግ ትምህርት ቤቱ በፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ፣ በነጻ የሕግ ድጋፍ፣ በአቅም ግንባታና በቴክኖሎጂ ልማት ዘርፎች ሰፊ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ 16 ነጻ የሕግ ድጋፍ ማዕከላት እንዳሉት የተናገሩት ዶክተር አስራት ፣ የውሃ ሕግና ሜዲኮ-ሊጋል የመሳሰሉ ልዩ የሕግ ፕሮግራሞችን እያስፋፋ እንደሚገኝ ጨምረው ገልጸዋል።
ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጋር የሚደረገው ይህ ትብብር የፍትሕ ሥርዓቱን በማዘመን፣ የሰው ኃይል አቅም በመገንባት፣ ለተማሪዎች የተግባር ልምምድ (ኢንተርንሺፕ) እድል በመፍጠርና የጋራ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አስታውቀዋል።
ዶ/ር አስራት አክለውም፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ለመሥራት የጀመረው አዲስ አሰራር በፍትሕ ሥርዓቱ እየተካሄደ ያለውን ሁለንተናዊ ለውጥ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸው፣ በጋራ የሚዘጋጁ የአጭር፣ መካከለኛና ረጅም ጊዜ እቅዶች ተቋማቱን ብቻ ሳይሆን ክልሉንና ሀገሪቱን የሚጠቅሙ ተምሳሌታዊ ውጤቶችን እንደሚያስገኙ ገልጸዋል።
ሁለቱ ተቋማት በጥናትና ምርምር፣ በዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥና የሕግ ትምህርት ጥራት ፣ በአቅም ግንባታ፣ በዲጂታል የፍትሕ አገልግሎቶች ልማት፣ በነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት፣ በአማራጭ የሙግት መፍቻ ሥርዓቶች ማጠናከር፣ አለምአቀፍ ጉባኤዎችን በትብብር ለማዘጋጀትና በሌሎች የክልሉን የዳኝነት እና የፍትሕ ስርዓት ማሻሻል በሚችሉ የጋራ ስራዎች ላይ በቅርበት ለመሥራት ተስማምተዋል።












