ባሕር ዳር ፣ ሰኔ 26/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)
የአማራ ክልል የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት የትብብር መድረክ በአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች ማጠናከሪያ አዋጅ፣ የሕግ መሰረት እንዲኖረው የተደረገ ሲሆን፣ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰብሳቢነት፣ የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ፣ የአማራ ክልል ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ እና የአማራ ክልል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን በጋራ የሚይዝ ነው።
የትብብር መድረኩ አባል ተቋማት ነጻነታቸውን ባከበረ መልኩ የፍትሕ አስተዳደሩን ውጤታማ ለማድረግ በሚያገናኟቸው የጋራ ጉዳዮች ላይ እቅድ በማውጣት የሚሰሩ ሲሆን፣ አፈጻጸሙን በሚመለከት አብይ ኮሚቴው በእየጊዜው እየገመገመ ሲሰራ ቆይቷል።
በዛሬው እለትም፣ የትብብር መድረኩ የ2018 ዓ ም የእቅድ አፈጻጸም እና የዘርፉ የአሻጋሪ እና ዘላቂ ልማት እቅድ የአንድ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት አመራሮች፣ ዳኞች፣ ዐ/ህጎች፣ የፖሊስ አባላት፣ ሌሎች ባለሙያዎች እና አጋር አካላት በተገኙበት ውይይት ተደርጎበታል።
የትብብር መድረኩ፣ የተቋማትን ሙያዊ ነጻነት እና ተጠያቂነት ማረጋገጥ፣ ሰብአዊ መብት ማክበር እና ማስከበር፣ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ውጤታማነት ማረጋገጥ፣ የአገልግሎት ቅልጥፍና ጥራት እና ውጤታማነት ማሳደግ፣ውጤታማ የሆነ የቴክኖሎጂ አቅርቦት እና ተጠቃሚነት፣ ቅንጅታዊ አሰራር፣ሙያዊ ስነ ምግባር መገንባት፣ ሙስና መከላከል እና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ፣ የአቅም ግንባታ ማጠናከር፣ የክርክር አቀራረብ እና አመራር ሥርዓት ማሻሻል፣ ማረም፣ ማነጽ እና ይቅርታ አሰጣጥ ስርዓትን ማሻሻል፣ የሪፎርም ሕጎችን አተገባበር ማጠናከር የሚሉ 11 አበይት ግቦችን በመያዝ ዝርዝር ተግባራትን በማቀድ ወደ ስራ የገባ ሲሆን፣በየዘርፉ የተሰሩ ስራዎች ዝርዝር ሪፖርት ቀርቧል።
የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት የ25 ዓመት አሻጋሪ እድገት እና ዘላቂ ልማት እቅድ ለመጀመሪያ ጊዜ እራሱን ችሎ በክልሉ ምክር ቤት ጸድቆ የአምስት ዓመት እና የአንድ አመት እቅድ ታቅዶ ወደ ሥራ የተገባ መሆኑ የሚታወስ ነው።
የዘርፉ የአሻጋሪ እና ዘላቂ ልማት እቅድ በዳኝነት እና የፍትሕ አካላት አመራሮች፣ ባለሙያዎች እና በሚመለከታቸው የዘርፉ ባለሙያዎች አማካኝነት የተዘጋጀ ሲሆን፣ በዛሬው እለትም የ2018 በጀት አመት አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
በዘርፋ የተያዙት ዋና አላማዎችም የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ እና ዘላቂ ሰላም መገንባት፣ የላቀ ፍትሕ አገልግሎት ማረጋገጥ እና የፍትሕ ተደራሽነት እና ሰብአዊ መብት ማረጋገጥ የሚሉ ሲሆኑ፣ ዝርዝር ተግባራቶችን በሚመለከት በዓመቱ በሁሉም የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማት የተተገበሩ ስራዎች በዝርዝር ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የዘርፎችን የ2018 በጀት ዓመት ሪፖርት ያቀረቡት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት አማካሪ እና የትብብር መድረኩ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ቢኒያም ዮሀንስ ሲሆኑ፣ ተሳታፊዎች በቀረበው ሪፖርት ላይ ሀሳብና አስተያይታቸውን ሰጠዋል።
የትብብር መድረኩ አባል ተቋማት መካከለኛ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የዳኝነት እና የፍትሕ መድረኩ በቅንጅት መስራቱ ተቋማቱ ፈጣን አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻሉን፣ በተቋማቱ መሪዎች እና ባለሙያዎች መካከል መልካም ግንኙነት እንዲኖር ማስቻሉን አንስተዋል።
የትብብር መድረኩ መቋቋም ሙያዊ ስልጠናዎችን በጋራ ማግኘት እንዲችሉ እንዳስቻላቸው የተናገሩት ተሳታፊዎቹ፣ይሄም ከትብብር መድረኩ ባለፈ ለተቋማቸው እና ለግል ህይወታቸው ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
ተሳታፊዎችን ከአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት እና ከትብብር መድረኩ ሰብሳቢ ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው ጋር ያወያዩት የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ሀላፊ አቶ ብርሀኑ ጎሽም፣ የአማራ ክልል ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) እና የአማራ ክልል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ኮሚሽነር ሀብታሙ ሲሳይ በተነሱ ሀሳብና አስተያይቶች ላይ ከተቋሞቻቸውና ከትብብር መድረኩ የጋር ስራዎች ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ አስተያይት ሰጠዋል።
መድረኩን ያጠቃለሉት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና የትብብር መድረኩ ሰብሳቢ ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው በበኩላቸው፣ የትብብር መድረኩ ተቀዳሚ አላማ ለፍትሕ ፈላጊው የክልሉ ህዝብ የተቀናጀ ፈጣን፣ ቀልጣፋ፣ እና አመኔታን ያተረፈ የዳኝነት እና የፍትሕ አገልግሎት በላቀ ትብብር መስጠት መሆኑን ገልጸው፣ ይሄንን እውን ለማድረግ ሁሉም የትብብር መድረኩ አባል ተቋማት፣ መሪዎች እና ባለሙያዎች በጀመሩት የላቀ ቁርጠኝነት እና የትብብር መንፈስ መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።















