ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

“የአማራ ክልል የዳኝነትና የፍትሕ ዘርፍ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበት ነው” ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው- የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት

“የአማራ ክልል የዳኝነትና የፍትሕ ዘርፍ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበት ነው” ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው- የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት

ባህር ዳር፣ ሰኔ 26/2018 ዓ.ም (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የአማራ ክልል የዳኝነትና የፍትሕ አካላት የትብብር መድረክ እና የዘርፉ የአሻጋሪ ዕድገትና ዘላቂ ልማት ዕቅድ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም የጋራ ግምገማ መድረክ ተካሂዷል።

መድረኩን የከፈቱት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት እና የትብብር መድረኩ ሰብሳቢ ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ የፍትሕ ተቋማት በተናጠል ሳይሆን በቅንጅትና በትብብር ሲሠሩ ለሕዝብ ፈጣን፣ ተደራሽ፣ ውጤታማና አመኔታን ያተረፈ የፍትሕ አገልግሎት መስጠት እንደሚቻል ገልጸዋል።

ክቡር ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት፣ በመስከረም 2017 ዓ.ም በጋራ ስምምነት የተጀመረው የትብብር ሥራ በኋላ በአዋጅ ቁጥር 297/2017 የሕግ ማዕቀፍ በማግኘት በክልል፣ በዞንና በወረዳ ደረጃ ተደራጅቶ ተጨባጭ ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል ብለዋል።

ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው አክለውም፣ በክልሉ የ25 ዓመት የአሻጋሪ ዕድገትና ዘላቂ ልማት ዕቅድ ውስጥ የዳኝነትና የፍትሕ ዘርፉ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በተለየ የዘርፍ ዕቅድ መካተቱ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ልዩ ትኩረት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸው፣ ለክልሉ መንግሥት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በ2018 በጀት ዓመት የተከናወኑ ሥራዎች ከቀደሙት ዓመታት የተሻለ አፈጻጸም ማሳየታቸውን የገለጹት ክቡር ፕሬዝዳንቱ፣ በሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያ፣ በሰው ኃብት ልማት፣ በዲጂታል የፍትሕ አገልግሎቶች፣ በስማርት ችሎት፣ በአማራጭ የግጭት መፍቻ ሥርዓቶች፣ በባህል ፍርድ ቤቶች፣ በየተቋማቱ የመረጃ መጋራት እና በተቀናጀ የወንጀል መከላከል ሥርዓት ግንባታ ከፍተኛ ለውጥ መመዝገቡን ጠቁመዋል።

የሕግና ፍትሕ ኢንስቲትዩት በድጋሚ በማደራጀት የልህቀት ማዕከል እንዲሆን እየተሠራ መሆኑን፣ የፖሊስ ኮሌጅ ወደ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ማደጉን ይህም የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን በስፋት እንዲያገኙ ማስቻሉን ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው ጨምረው ገልጸዋል።

በትብብር መድረኩ በኩል የክልል አቀፍ የተቀናጀ የወንጀል መከላከል ስትራቴጂ፣ የዳኝነትና የፍትሕ አካላት የመረጃ ማዕከል ማቋቋሚያ እና የመረጃ መጋራት ስምምነት መዘጋጀታቸው በቀጣይ የፍትሕ አስተዳደሩን የበለጠ ውጤታማ እንደሚያደርጉትም ገልጸዋል።

የፍትሕ ዘርፉ የመጨረሻ ግብ ውጤታማ ፍትሕን ለሕዝብ ማረጋገጥ መሆኑን የገለጹት ክቡር ፕሬዝደንቱ፣ ሁሉም የዘርፉ ተቋማት የተጀመረውን መልካም የትብብር ሥራ በማጠናከር ለጋራ ዓላማ በተቀናጀ መንገድ እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *