ባህርዳር፣ ሰኔ 25/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተገልጋዩን ወጭ፣ እንግልት፣ ጊዜ እና ጉልበት የቀነሰ፤ ፈጣን፣ ቀልጣፋ፣ ዘመናዊ እና ተገማች የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት በሁሉ አቀፍ የለውጥና የአሰራር ማሻሻያ ላይ ይገኛል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፣ አሰራሮቹን በማጠናከር አገልግሎቱን በላቀ ጥራትና ተደራሽነት ለማቅረብ፣ እና በሌሎች የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ማሻሻያዎች ላይ በአጋርነት እና በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን ውይይት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ ከአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝደንት ሸኽ ኑረዲን ቃሲም ጋር አድርገዋል።
የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸኽ ኑረዲን ቃሲምና ሌሎች የምክር ቤቱ አመራሮችን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው ያነጋገሩት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሸርያ ፍርድ ቤቶችን ጨምሮ የክልሉን ፍርድ ቤቶች የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ በተጨባጭ ለማሻሻል የተተገበሩ እና እየተተገበሩ ያሉ ለውጦችን በሚመለከት ገለጻ አድርገውላቸዋል።
ከውይይቱ በተጨማሪ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ምቹ የስራ ከባቢ እና ዘመናዊ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ተዘዋውረው የጎበኙት ሸኽ ኑረዲን ቃሲም፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በጀመራቸው የለውጥና የማሻሻያ ስራዎች መደነቃቸውን ገልጸው፣ በሸርያ ፍርድ ቤቶች እና በሌሎች የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ስራዎች ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጋር በትብብር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።












