ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

የአማራ ክልል የዳኝነት እና የፍትሕ ዘርፍ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች አካል ጉዳተኞች በፍትሕ ስርዓቱ ላይ ሊኖራቸው ስለሚገባ እኩል የመሳተፍ መብት ተወያዩ

የአማራ ክልል የዳኝነት እና የፍትሕ ዘርፍ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች አካል ጉዳተኞች በፍትሕ ስርዓቱ ላይ ሊኖራቸው ስለሚገባ እኩል የመሳተፍ መብት ተወያዩ

ባሕር ዳር፣ ሰኔ 20/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

በዳኝነትና በፍትህ ዘርፍ እየተተገበሩ ያሉ የለዉጥ ሥራዎች እና የዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ ዉጤታማነት ለማሳደግ የሚወሰዱ ተሞክሮዎች በሚል ርዕስ በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አዘጋጅነት በተካሄደው ወርክሾፕ በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ስልጠናዎችና የውይይት መነሻ ጽሁፎች ሲቀርቡ ውለዋል።

በወርክሾፑ የከሰዓት ውሎም፣ የፍትህ ተደራሽነትን ለማሳደግ ሊወሰዱ የሚገባቸው ስትራቴጅክ እርምጃዎች እና የተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር በሚል ርዕስ የውይይት መነሻ ሀሳብ የጎንደር ዩኒቨርስቲ ረዳት ፕሮፌሰር በሆኑት ሞላልኝ በላይ (ዶ/ር)፣ አማካኝነት ቀርቧል።

ትኩረቱን የፍትሕ ስርዓቱ ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ መሆኑን ማረጋገጥ ላይ ያደረገ ጽሁፍ የቀረበ ሲሆን፤ ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ የሆነ የፍትሕ ሥርዓት አለ ለማለት የፍትሕ ተቋማት ህንጻዎች ለአካል ጉዳተኞችን ምቹ መሆንን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን በፍትሕ ሂደቶች ውስጥ እኩል ተሳትፎ ያላቸው መሆኑን ማረጋገጥንም የሚጨምር ስለመሆኑ ተነስቷል፡፡

ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ ያልሆኑ የፍትሕ ተቋማት ሕንጻዎች፣ በፍትሕ ተቋማት የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ አለመኖር፣ በብሬል የተዘጋጁ የሕግ ሰነዶች እጥረት እና ለዳኞች፣ ዐ/ህጎች ፣ለፖሊሶች፣ እና ሌሎች የፍትሕ ሥርዓት ተሳታፊዎች አካል ጉዳተኝነትን አስመልክቶ በቂ የግንዛቤ ስልጠና አለመሰጠቱ በዘርፉ የሚነሱ ችግሮች መሆናቸው ተነስቷል፡፡

ተደራሽነትን ለማረጋገጥ አካላዊ መሰረተ ልማት ማሻሻያዎች እና የሥርዓት ማሻሻያዎች ሊደረጉ የሚገባ ስለመሆኑ ጽሁፍ አቅራቢው ዶክተር ሞላልኝ አንስተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም፣ በወንጀል ምርመራ ሂደት የፖሊስ እና ዐ/ህግ ሚና በሚል ርዕስ ሌላ ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦ ሀሳብና አስተያየት ተሰጦበታል።

ጥናታዊ ጽሁፉን ያቀረቡት፣ በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሰቲ የፒ.ኤች .ዲ ፕሮግራም አስተባባሪ ዋና ኢንስፔክተር መዳረሻዉ ታፈሰ (ዶ/ር) እና በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሰቲ የህግ ትምህርት ክፍል ሀላፊ ዋና ኢንስፔክተር ትንሳኤ ገብረክርስቶስ

ሲሆኑ፣ በወንጀል ምርመራ ሂደት ውስጥ የዘርፉ ተቋማት ሊኖራቸው የሚገባውን ኃላፊነት የተመለከተ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል።

በቀረቡት የውይይት መነሻ ሀሳቦች ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ በውይይቱ ማጠቃለያ የሰጡት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘደንት ክቡር አቶ አለም አንተ አግደው፣ የዲጂታል ፍትሕ አገልግሎት ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ የሚሆንበትን አግባብ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሚሰራበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *