ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

ፈታኝ ሁኔታዎች ባሉ ጊዜ ህግና ስርዓት በማጽናት የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማት ሚና በሚል ርእስ ለአማራ ክልል የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ስልጠና ተሰጠ

ፈታኝ ሁኔታዎች ባሉ ጊዜ ህግና ስርዓት በማጽናት የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማት ሚና በሚል ርእስ ለአማራ ክልል የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ስልጠና ተሰጠ

ባህርዳር፣ ሰኔ 20/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የክልሉን የዳኝነት እና የፍትሕ ስርዓት በዘላቂነት በማሻሻል ህብረተሰቡ እምነት የሚጥልባቸው፣ በክልሉ የልማት እና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የበኩላቸውን ሚና መወጣት የሚችሉ የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማትን ለመገንባት ከሌሎች የፍትሕ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እና በቅንጅት እየሰራ ይገኛል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይዞት የተነሳውን ርዕይ እውን ማድረግ በሚያስችለው የዳኝነት እና የፍትሕ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ትግበራ የእስካሁን አፈጻጸም እና ቀጣይ የትብብር አቅጣጫ ላይ ከክልሉ ፍትሕ ቢሮ፣ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ እና ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ጋር የተወያየ ሲሆን፣ በውይይቱ ላይ ፈታኝ ሁኔታዎች ባሉ ጊዜ ህግና ስርዓት በማጽናት የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማት ሚና በሚል ርዕስ ስልጠና ተሰጧል።

ስልጠናውን የሰጡት በአዲስ አባባ ዩኒቨርስቲ ሕግ ትምህርት ቤት ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት የሕግ አማካሪ እና ተመራማሪው ዮናስ ተስፋ (ዶ/ር) ናቸው።

ዶክተር ዮናስ፣ የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማት ፈታኝ ሁኔታዎች ባሉበት ወቅት በአስቻይ ሁኔታዎች ከሚያስፈልጉበት በላይ እንደሚያስፈልጉ ገልጸው፣ በችግር ወቅት እና ከችግሩ ማግስት ህግና ስርዓትን የማስፈን ሀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

በተለያየ ጊዜ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጽናት ለማለፍ የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማት ጥንካሬ ወሳኝ ነው ያሉት ዶክተር ዮናስ፣ ተቋማቱ አንዱ ባንዱ ላይ ሳይነሳ፣ ከውድድር በነጻ መንፈስ እና በላቀ ትብብር ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

ጠንካራ የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማት ያላቸው ሀገራት የከፋ ችግር እንደማይገጥማቸው በገለጻቸው ያብራሩት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ እነዚህ ተቋማት በችግር ጊዜ የመረጋጋት መልህቅ ናቸው ብለዋል።

የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማት ፈታኝ ሁኔታዎች ባሉበት ወቅትም በሙሉ አቅማቸው ስራ ላይ ሊሆኑ እንደሚገባ ያስረዱት ዶክተር ዮናስ፣ ህገወጥነት እንዳይባባስ፣ ህግ እና ስርዓት በግለሰቦች እጅ ላይ እንዳይወድቅ እና ሴቶች እና ህጻናትን ጨምሮ የሌሎች ንጹሀን መብት እንዳይጣስ የማድረግ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው ብለዋል።

የክልሉን የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማት ጠንካራ ለማድረግ እና አሰራራቸውን ለማዘመን በርካታ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ማየታቸውን የተናገሩት ዶክተሩ፣ እየተተገበሩ ያሉ ዘመናዊ የዳኝነት እና የፍትሕ አገልግሎት መስጫ መሰረተ ልማቶች፣ እንዲሁም የዳኞችን እና ሌሎች የፍትሕ አካላትን አቅም ለማሳደግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *