ባህርዳር ፣ ሰኔ 20/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የክልሉን የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል እየወሰዳቸው ካሉ ስር-ነቀል የለውጥ ስራዎች አንዱ የዳኞችን፣ የጉባኤ ተሿሚዎችን እና የሰራተኞችን ሙያዊ እና ስነ-ምግባራዊ አቅም ማሳደግ ነው።
በክልሉ የዳኝነት እና የፍትሕ ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ካስፈለገ ሁሉም የዘርፉ ተዋናዮች በጋራ ትብብር መስራት አለባቸው የሚለው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ጨምሮ፣ ከክልሉ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ፣ ፍትሕ ቢሮ እና ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ከተወጣጡ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ጋር ዘርፉ ለክልሉ ማህበረሰብ እየሰጠ ያለውን አገልግሎት በላቀ ደረጃ ለማቅረብ እስካሁን በተሰሩ የጋራ ስራዎች እና በቀጣይ የትብብር መስኮች ላይ የሚመክር ወርክሾፕ አዘጋጅቷል።
በወርክሾፑ ላይ ከተለያዩ ተቋማት የተወጣጡ የሕግ ምሁራን ስልጠናዎችን የሰጡ እና የውይይት መነሻ ጽሁፎችን ያቀረቡ ሲሆን፣ ተሳታፊዎችም በቀረቡ ጽሁፎች መነሻነት ውይይቶችን አካሂደዋል።
ለዳኝነት እና የፍትሕ ዘርፉ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ስልጠና ከሰጡት የህግ ምሁራን መካከልም፣ የወንጀል ፍትሕ ፕሮፌሰሩ ፔትሮ ቶጃ አንዱ ናቸው።
በፔንስልቫንያ (ዩናይትድ ስቴትስ) በሚገኘው የኩተዝታውን ዩኒቨርሲቲ የወንጀል ፍትህ ትምህርት ክፍል ለ27 ዓመታት ያስተማሩት ፕሮፌሰር ፔትሮ ቶጃ፣ከዳኝነት እና የፍትሕ አካላት መሪዎችና ባለሙያዎች የሚጠበቅ ሙያዊ ስነ-ምግባር በሚል ርዕስ ስልጠና ሰጠዋል።
ከአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች በተጨማሪ በጣሊያን እና ሌሎች ሀገሮች በሚገኙ በርካታ ዩኒቨርስቲዎች ያስተማሩት ፕሮፌሰሩ፣ ያገኙትን ልምድ እና እውቀት ለክልሉ የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች አጋርተዋል።
የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት ካለባቸው ህዝባዊ አደራ የሚመነጭ ከፍተኛ የሆነ የሙያዊ ስነ-ምግባር ባለቤት መሆን ይጠበቅባቸዋል ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ ይህንን ሕዝባዊ አመኔታ ለማስጠበቅ ሁሉም የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት ማህበረሰባቸውን በላቀ የሙያ ስነ-ምግባር ማገልገል ይኖርባቸዋል ብለዋል።
የዳኝነት እና የፍትሕ አካላትን ሙያዊ ስነምግባር ምንነት እና አስፈላጊነት የአሜሪካን ጨምሮ የሌሎችን ሀገራት ተሞክሮ እያነሱ ለተሳታፊዎች ገለጻ ያደረጉት ፕሮፌሰሩ፣ የተለያዩ ምሁራን በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ፍልስፍናዊ አተያይም ለውይይት ያቀረቡ ሲሆን፣ ተሳታፊዎችም በጉዳዩ ላይ ያሏቸውን ጥያቄዎች እና አስተያይቶች አንስተውላቸዋል።
ፕሮፌሰር ፔትሮ፣ ከዳኝነት እና የፍትሕ አካላት ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች በተጨማሪ፣ ለአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች በዳኝነት ሙያዊ ስነ-ምግባር ላይ ስልጠናዎችን ሰጠዋል።
ህብረተሰቡ በህይወቱ፣ በንብረቱ እና በነጻነቱ ላይ ወሳኝ አድርጎ የሾማቸው ዳኞች በላቀ የስነ-ምግባር ደረጃ ላይ መገኘት አለባቸው ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ ይሄንን በማረጋገጥ ለሙያቸው ክብር የመቆም ታሪካዊ ሸክም ተጥሎባቸዋል ብለዋል።
ዳኞች በእለት ከእለት እንቅስቃሴያቸው እና በማህበራዊ መስተጋብራቸው ጭምር ህብረተሰቡ ከእነሱ የሚጠብቀው የስነ ምግባር ልእልና አለ ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ ይሄንን አስጠብቆ መዝለቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቅምን ጨምሮ አንዳንድ ገደቦች የዳኝነት ሙያን ክብር ለመጠበቅ እና የዳኞችን ገለልተኛነት በማረጋገጥ ህብረተሰቡ የሚሰጡ ውሳኔዎች ከወገንተኝነት ነጻ ሆነው የተሰጡ በመሆናቸው በፍርድ ቤቶች ላይ እምነት እንዲያድርበት የሚቀመጡ ገደቦች መሆናቸውን በስልጠናቸው ያነሱት ፕሮፌሰር ፔትሮ፣ ገደቦቹ አሜሪካን ጨምሮ በሌሎች ሀገራት ዳኞች ላይም የሚተገበሩ መሆናቸውን አንስተዋል።
ስልጠናውን የተከታተሉ ዳኞችና የጉባኤ ተሿሚዎች ከዳኝነት ሙያዊ ስነ-ምግባር ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጥያቄዎች ያነሱ ሲሆን፣ በዘርፉ በንባብ ፣ በስራ እና በህይወት ልምድ የካበተ እውቀት ያላቸው ፕሮፌሰር ፔትሮ ቶጃ ምላሽና ማብራሪያ ሰጠዋል።







