ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

በአማራ ክልል የዳኝነት እና የፍትሕ ዘርፍ አገልግሎት አሰጣጥ አተገባበር እና የቀጣይ ትብብር አቅጣጫዎች ላይ የሚመክር ወርክሾፕ ተካሄደ

በአማራ ክልል የዳኝነት እና የፍትሕ ዘርፍ አገልግሎት አሰጣጥ አተገባበር እና የቀጣይ ትብብር አቅጣጫዎች ላይ የሚመክር ወርክሾፕ ተካሄደ

ባህርዳር ፣ ሰኔ 20/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

በአማራ ክልል በዳኝነትና ፍትሕ ዘርፍ እየተተገበሩ ያሉ የለውጥ ሥራዎችን፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ውጤታማነትን እና የቀጣይ የትብብር አቅጣጫዎችን በሚመለከት በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አዘጋጅነት የዳኝነት እና የፍትህ አካላት ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ጋር የሚመክር ወርክሾፕ ተካሂዷል።

ወርክሾፑን በንግግር የከፈቱት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ በክልሉ ለሦስት ዓመታት ሲተገበር የቆየው የዳኝነትና የፍትሕ ትራንስፎርሜሽን እቅድ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ገልጸው፣ በትግበራው የተገኙ ስኬቶችን እና ክፍተቶችን በመገምገም ቀጣይ የሚሠሩ ሥራዎችን ለመለየት ወርክሾፑ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

በክልሉ የዳኝነት እና የፍትሕ ዘርፍ በሰው ኃይል አቅም ግንባታ፣ በተቋም ግንባታ፣ በመረጃ አያያዝ እና በፍትሕ ተደራሽነት መስኮች ጉልህ ለውጦች መመዝገባቸውን የጠቀሱት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ የክልሉ የሕግና ፍትሕ ኢንስቲትዩት እንደገና ተደራጅቶ የክልሉ የሕግና ፍትሕ ተቋማት የልህቀት ማዕከል እንዲሆን መሰራቱን እና የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማት የመረጃ ማዕከል ሆኖ እንዲያገለግል ሥልጣን መሰጠቱን ገልጸዋል።

የፍትሕ ተደራሽነትን ለማስፋፋት በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን የተናገሩት ክቡር ፕሬዝደንቱ፣ አማራጭ የሙግት መፍቻ ሥርዓቶች ለማጠናከር የባሕል ፍርድ ቤቶች በበርካታ የክልሉ ቀበሌዎች መቋቋማቸውን እና የሕግ ድጋፍ አገልግሎት እንዲስፋፋ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የተከላካይ ጠበቆች እራሱን የቻለ ክፍል እንዲኖረው መደረጉን አስታውቀዋል።

የዳኝነት ነፃነትና ገለልተኝነትን ለማጠናከር የዳኞች ያለመከሰስ መብት በአዋጅ መፅደቁን እና የዳኝነትና የፍትሕ አካላት የትብብር መድረክ በአዋጅ መቋቋሙን የጠቀሱት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ ይህም በዳኞች ላይ ይደርሱ የነበሩ ያልተገቡ ጫናዎችን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።

በዳኝነት እና የፍትሕ ዘርፉ የተቀናጀ ስራ አበረታች ለውጦች ቢመዘገቡም፣ ማህበረሰቡ የሚጠብቀውን ደረጃ ለመድረስ ገና በርካታ ሥራዎች እንደሚቀሩ የጠቆሙት ክቡር ፕሬዝደንቱ፣ የዳኝነትና የፍትሕ ተቋማት ቀጣይ ትብብር የተጀመሩ መልካም ስራዎችን በስኬት ለማጠናቀቅ ወሳኝ መሆኑን አሳስበዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *