ባህርዳር፣ ሰኔ 16/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በጥናት ለለያቸው 15 የክልሉ ያለመግባባት መፍቻ ዘዴዎች የክልሉ የባሕል ፍርድ ቤቶች ሆነው እንዲሰሩ እውቅና መስጠቱ እና በይፋ ስራ ማስጀመሩ ይታወቃል፡፡
በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች ለሚገኙ የባሕል ፍርድ ቤቶች ሽማግሌዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት በይፋ ስራ ያስጀመረው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፣ ከደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎ እና የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞኖች ለተወጣጡ የባሕል ፍርድ ቤት ሽማግሌዎችም ተመሳሳይ የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት ጀምሯል፡፡
በስልጠናው ማስጀመሪያ መረሀግብር የተገኙት የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ መኮነን፣ የመደበኛ ፍርድ ቤቶችን ስራ የሚያግዙ አማራጭ የሙግት መፍቻ ስርዓቶች አስፈላጊ ናቸው ብለዋል፡፡
የማህበረሰቡን የፍትህ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ከክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጀምሮ በተዋረድ ያሉ ፍርድ ቤቶች በርካታ ስራዎችን እየሰሩ መሆናቸውን እና አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው፣ ነገር ግን በመደበኛ ፍርድ ቤቶች በሚሰጠው የዳኝነት አገልግሎት ብቻ የማህበረሰቡን ፍላጐት ማሟላት ስለማይቻል አማራጭ የሙግት መፍቻ ስርዓቶችን መዘርጋት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የባሕል ፍርድ ቤቶች ሕጋዊ እውቅና እንዲያገኙ በማድረግ እና አስፈላጊውን የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት ስራ ማስጀመሩ የሚያስመሰግን ተግባር ነው ያሉት አቶ አሊ፣ ሰልጣኞች ከስልጠናው የሚያገኙትን ተጨማሪ እውቀት በተግባር ካዳበሩት ክህሎት ጋር በማዋሃድ፣ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚፈጠሩ አለመግባባቶች በአቅራቢያቸው ያለ ምንም ወጪ እና እንግልት መፈታት እንዲችሉ የተጣለባቸውን አደራ በታማኝነት እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክብርት ወ/ሮ ትዕግስት ዳኛቸው በበኩላቸው፤ የባሕል ፍርድ ቤቶች ህጋዊ እውቅና እንዲያገኙ ከማድረግ ጀምሮ ለማህበረሰቡ ግንዛቤ መፍጠርን፣ ሽማግሌዎችን የማስመረጥ፣ የበጎ ፈቃድ ጸሀፊዎችን የመቅጠር እና የማስቻያ ቦታዎችን የማመቻቸት ሂደትን ጨምሮ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትና በተዋረድ ባሉ ፍርድ ቤቶች የተከናወኑ ዝርዝር ተግባራትን ለተሳታፊዎች አብራርተዋል።
በክልሉ ከ1 ሺህ 228 በላይ ቀበሌዎች ላይ የባሕል ፍርድ ቤት ዳኞችን ማስመረጥ መቻሉን የገለፁት ወ/ሮ ትዕግስት፤ ስልጠናው የባሕል ፍርድ ቤቶቹ ወደ ተሟላ ሥራ ከመግባታቸው በፊት አባላቱ ሕጋዊ አሠራሩንና ኃላፊነታቸውን እንዲረዱ ለማስቻል የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለስልጠናው መሳካት ድጋፍ ያደረገውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ድርጅቶች ህብረትን ያመሰገኙት ወ/ሮ ትዕግስት፣ ድጋፉ በቀጣይም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ድርጅቶች ህብረት ተወካይ አቶ አክሊሉ አደራጀው በበኩላቸው፤ ህብረቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ እየሰራቸው ያሉትን ተግባራት ለስልጠናው ተሳታፊዎች አብራርተዋል።
ስልጠናው በዋናነት በአማራ ክልል የባሕል ፍርድ ቤቶችን እውቅና ለመስጠት እና ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 298/2017 እና አዋጁን ለማስፈጸም በወጣው መመሪያ ቁጥር 23/2018 ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ በስልጠናው የመጀመሪያ ቀን ውሎ፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የባሕል ፍርድ ቤቶች አማካሪ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይማም ሰይድ፣ በአማራ ክልል ባሕላዊ ያለመግባባት መፍቻ መንገዶች ላይ የተደረገ ዝርዝር ጥናትን የተመለከተ ስልጠና ሰጠዋል፡፡
የስልጠና መድረኩ፣ ከሰኔ 15 እስከ ሰኔ 17 ቀን 2018 ዓ.ም ለሶስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲሆን፣ የባሕል ፍርድ ቤት ሽማግሌዎቹ ስራቸውን በአግባቡ ማከናወን የሚያስችላቸውን ተጨማሪ አቅም የሚያገኙበት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ዘገባው የደቡብ ወሎ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው፡፡











