ባህርዳር፣ ሰኔ 13/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አገልግሎት አሰጣጡን ዘመናዊ ፣ ቀልጣፋ፣ ወጭ እና ጊዜ ቆጣቢ ማድረግ የሚያስችሉ የዲጅታላይዜሽን ፣ ምቹ የስራ ከባቢዎችን እና ሌሎች ቀልጣፋ የዳኝነት አገልግሎት መስጫ መሰረተ ልማቶችን በሁሉም የክልሉ ፍርድ ቤቶች በማስፋፋት ላይ ይገኛል።
በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የተጀመሩ የዘመናዊ አገልግሎት መስጫ መሰረተ ልማቶች በየደረጃው ባሉ ፍርድ ቤቶች በመስፋፋት ላይ ሲሆኑ፣ ከፍተኛ እና ወረዳ ፍርድ ቤቶችም ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይዞት የተነሳውን ርእይ ለማስቀጠል የተጀመሩ የዲጅታላይዜሽን እና ሌሎች የለውጥና የማሻሻያ ስራዎችን በማስፋፋት ላይ ናቸው።
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን የለውጥ ስራዎች ከሌሎች የክልሉ ከፍተኛና ወረዳ ፍርድ ቤቶች እኩል እያስቀጠሉ ካሉት ፍርድ ቤቶቻችን አንዱ የሆነው የምስራቅ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዲጅታላይዜሽን፣ የፕላዝማ ችሎት፣ ስማርት ችሎት፣ የዜጎችን በግልጽ ችሎት የመዳኘት ህገ መንግስታዊ መብት እያረጋገጡ ያሉ የግልጽ ችሎት ማስቻያ አዳራሾችን፣ ተገልጋዮች ጉዳያቸውን በአንድ ቦታ የሚጨርሱበት የአንድ ማእከል ዲጅታል አገልግሎት እና ሌሎች ቀልጣፋ የዳኝነት አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶችን በመዘርጋት እና በማስፋፋት ላይ ይገኛል።
የለውጥ ስራዎች የደረሱበትን ደረጃ እና ለተገልጋዩ እየሰጡት ያለውን ወጭ፣ ጉልበት፣ እና ጊዜ ቆጣቢ፣ ፈጣን፣ ቀልጣፋ እና ተገማች አገልግሎት የምስራቅ ጎጃም ዞን መስተዳደር እና የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር አመራሮች ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸዉም በከፍተኛ ፍርድ ቤቱ የዲጂታላይዜሽን ስራዎች፣ የፕላዝማ ችሎቶች፣ስማርት ችሎቶች፣ ግልፅ ችሎት የሚሰጥባቸዉን አዳራሾች ፣ የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጥበት አንድ ማዕክል እና የኢ-ፋይልንግ ስራዎች የሚሰሩበትን ክፍሎችና አጠቃላይ አገልግሎት አሰጣጡን ፈጣንና ቀልጣፋ እንዲሆን ለማስቻል የተሰሩ አደረጃጀቶችን ተመልክተዋል፡፡
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ እየተገበራቸው ስለሚገኙና ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ላይ ተደራሽ እየሆኑ ስለሆኑ ሁሉን አቀፍ የለውጥ ስራዎች ፣እንዲሁም ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ እየሰራቸው ያሉ ስራዎችን በተመለከተ በከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት፣የስራ ሂደት አስተባባሪዎችና የአይሲቲ ባለሙያዎች ገለፃ ተደርጎላቸዋል፡፡
በጉብኝቱ የተገኙት የምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪና የክልል ምክር ቤት አባሉ አቶ ኑርልኝ ብርሃኑ፣ የከፍተኛ ፍ/ቤቱን የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋ፣ ዘመናዊና ተደራሽ ለማድረግ በከፍተኛ ፍርድ ቤቱ እየተሰራ ያለው ስራ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን የለዉጥ ጉዞ ፈለግ የተከተለና የለውጥ ስራው ተጨባጭና የሚታይ እንዲሆን ያስቻለ በመሆኑ የሚበረታታና ለሌሎች ተቋማትም የተሞክሮ ማዕከል የሚሆን ነው ብለዋል፡፡
በተቋሙ ላይ የደረሰውን ውስጣዊና ውጫዊ ጉዳት በራስ አቅም መልሶ በማደራጀትና እድሳት በማድረግ ወደነበረበት ተቋማዊ ቁመና በመመለሱ ረገድ የተሰራው ሰራ፣እንዲሁም ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ በወረዳ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶች፣በዳኞችና በጉባኤ ተሿሚዎች ላይ የሚታዩ የስነ ምግባር ግድፈቶችን እየተከታተለ የሚያርምበት መንገድ አርዓያነት ያለውና ሌሎች ተቋማትም ትምህርት የሚወስዱበት መሆኑን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው፣ በተቋሙ ውስጥ ግንባታቸው ያላለቁ የህንጻ መወጣጫ አሳንሰር እና የአዳራሽ ወንበሮች እንዲሟሉ ከክልሉ መንግስት እና ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጋር በመነጋጋር እልባት እንዲሰጠዉ የበኩላችንን ኃላፊነት እንወጣለን ብለዋል፡፡
የደብረማርቆስ ሬጅኦ ፖሊታንት ከተማ አስተዳደር ከንቲባ እና የህዝብ ተወካዮች የምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ተሾመ ዋለ በበኩላቸዉ፣ ተቋሙን ለአገልግሎት አሰጣጥ ምቹ በማድረግ አገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ ፣ወጭ እና ጊዜ ቆጣቢ እንዲሆን ለማድረግ የተሰራው ስራ ፣ እንዲሁም መዝገቦች የተደራጁበት መንገድ ፍርድ ቤቱ የህዝብ አመኔታን እንዲያተርፍ ያስቻሉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ከሌሎች ተቋማት ጋር ተቀራርቦ ለመስራት እያሳዬ ያለው ቁርጠኝነትም በመካከል ያለውን መገፋፋት ያስቀረ ነው ብለዋል፡፡
በጉብኝታቸው ማጠቃለያም፣ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱንም ሆነ በስሩ ያሉ ወረዳ ፍርድ ቤቶችን በመደገፍና በማገዝ የተጀመረው የለውጥ ስራ ውጤታማ እንዲሆን የተቻላቸዉን ሁሉ እንደሚያደርጉ መናገራቸውን ከምስራቅ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፌስ ቡክ ገጽ የተገኘው ዘገባ ያስረዳል።








