ባህርዳር፣ ሰኔ 11/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የክልሉን የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ያለው፣ ቀልጣፋ፣ ዘመናዊ፣ተደራሽ፣ ጊዜ እና ወጪ ቆጣቢ በማድረግ፣ ፍርድ ቤቶች የህዝብ አመኔታን ያተረፉ እንዲሆኑ የሚያስችል የለውጥ እና የማሻሻያ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል።
በተለያየ ጊዜ ከፌደራል እና ከክልል የሚመጡ እንግዶች የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን የለውጥ ስራዎችን ለመመልከት የቻሉ ሲሆን፣ በዛሬው እለትም የፍርድ ቤት ጉዳዮች አዘጋገብ እና የፍርድ ቤት የማሻሻያ እና የለውጥ ስራዎች ላይ ለመወያያት በጠቅላይ ፍርድ ቤት የተገኙት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለሙያ ሴቶች ማህበር የአማራ ክልል አባላት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን የለውጥ ስራዎች ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸውም፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት የዲጂታላይዜሽን ስራዎች እና ስማርት ችሎቶችን፣ የዲጂታል አንድ ማእከል አገልግሎት፣ ግልጽ ችሎት የሚከናወንባቸውን የችሎት አዳራሾች፣ የጥሪ ማእከል እና ሌሎች የለውጥና ማሻሻያ ስራዎችን ተመልክተዋል።
በተሰሩ የማሻሻያ ስራዎች መደነቃቸውን የገለጹት የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎቹ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የስማርት ችሎት አገልግሎት እና የኢ- ፋይሊንግ አገልግሎት በመስጠት ዜጎች ከዚህ ቀደም ፍትህ ለማግኘት ይደርስባቸው የነበረውን እንግልት እና ወጪ በማስቀረት ፍትሕን ተደራሽ በማድረግ ህግ መንግስታዊ ሀላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ባሻገር በጠቅላይ ፍርድ ቤት ባህር ዳር ምድብ ችሎት ጉዳይ ኖሯቸው በአካል ለሚመጡ እና ህፃናት ለያዙ እናቶች እራሱን የቻለ ማረፊያ ማዘጋጀቱ ሰብአዊነት የሚሰማው ተግባር መሆኑን እና ባለጉዳዮች ተቋሙን በእኔእነት እና በባለቤትነት ስሜት እንዲገለገሉበት የሚያስችል ስራ መሆኑን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰራቸው ስራዎች ክልሉን እና የክልሉን ማህበረሰብ የሚመጥኑ ሆነው አግኝተናቸዋል ያሉት ባለሙያዎቹ፣ ሌሎች ተቋማትም የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን አርአያነት ያለው ስራ በተሞክሮነት በመጠቀም ለተገልጋዮቻቸው ምቾትን የሚሰጡ ፣ የተገልጋይን እርካታ ማረጋገጥ የሚችሉ ተቋማትን እንዲገነቡ እና ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶችን እንዲዘረጉ ጠይቀዋል።












