ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለሙያ ሴቶች ማህበር ጋር በመተባበር በፍርድ ቤት ጉዳዮች አዘጋገብ እና በፍርድ ቤቶች የለውጥ ሂደት ላይ ስልጠና ሰጠ

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለሙያ ሴቶች ማህበር ጋር በመተባበር በፍርድ ቤት ጉዳዮች አዘጋገብ እና በፍርድ ቤቶች የለውጥ ሂደት ላይ ስልጠና ሰጠ

ባህርዳር ፣ ሰኔ 11/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የክልሉን የዳኝነት እና የፍትሕ ስርዓት በመሰረታዊነት በማሻሻል ተገልጋዩ እምነት የሚጥልበት፣ በእኔነት ስሜት የሚጠቀምበት እና ዘመናዊ የዳኝነት አገልግሎት የሚያገኝበት ተቋም በመገንባት ላይ ይገኛል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የተገልጋዮችን ወጭ፣ እንግልት፣ ጊዜ እና ጉልበት በመቀነስ፣ በአካልም፣ በአገልግሎት ጥራትም ለህብረተሰቡ ተደራሽ የሆኑ ፍርድ ቤቶችን በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ለማረጋገጥ የሚያደርገው ጥረት ተገልጋዩ ህብረተሰብ ዘንድ እንዲደርስና ህብረተሰቡ የአገልግሎቱ ተጠቃሚና ባለቤት እንዲሆን በማስተዋወቅና ሰፊ የግንዛቤ ፈጠራ በመፍጠር ደግሞ መገናኛ ብዙሀን ከፍተኛውን ድርሻ በመወጣት ላይ ናቸው።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፣ መገናኛ ብዙሀን የፍርድ ቤት ጉዳዮችን በሚመለከት የሚሰሯቸው ዘገባዎች የፍርድ ቤት የዳኝነት አካሄድ መርሆዎችን ያከበረ እንዲሆን ለማስቻል የፍርድ ቤት ጉዳዮችን በምን አግባብ እና እንዴት መዘገብ እንዳለባቸው የሚያስገነዝብ እና የፍርድ ቤቶች የለውጥና የማሻሻያ ስራዎች ላይ ለኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለሙያ ሴቶች ማህበር የአማራ ክልል አባላት ስልጠና ሰጧል።

ስልጠናውን ያስጀመሩት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ ፍርድ ቤቶች እና መገናኛ ብዙሀን ተቀራራቢ በሆነ የሙያ ስነምግባር የሚመሩ እና በአንድ ሀገር የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ፣ የህግ የበላይነት መስፈን አንዲሁም የማህበራዊ እና የእኩልነት መብት መረጋገጥ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ተቋማት ናቸው ብለዋል።

ስልጠናውን ስናዘጋጅ የዳኝነት እና የጋዜጠኝነት የሙያ ስነምግባርን መሰረት ባደረገ መልኩ በቀጣይነት ለአንድ አላማ ተባብረን እና ተቀራርበን መስራት እንድንችል ነው ያሉት ክቡር ፕሬዝዳንቱ፣ ፍርድ ቤቱ የክልሉን የዳኝነት እና አጠቃላይ የፍትሕ ስርዓት በመሰረታዊነት በማሻሻል ተገልጋዮች እምነት የሚጥሉበት፣ የንግድና የኢንቨስትመንት ጉዳዮች የንግድ ሚስጥራቸው ተጠብቆ በአጠረ እና በተፋጠነ ጊዜ ጉዳያቸው የሚታይበትን አማራጭ የዳኝነት ስርዓት ለመዘርጋት፣ ዘመናዊ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥን በሁሉም የክልሉ ፍርድ ቤቶች ደረጃ በደረጃ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ተናግረው፣ የተጀመሩ ለውጦች ህዝባዊ እንዲሆኑ እና ህብረተሰቡ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆን የማንቃት እና የማስተዋወቅ ስራ የመገናኛ ብዙሀን ነው ብለዋል።

ስልጠናው መገናኛ ብዙሀን የፍርድ ቤቶችን ነጻነት እና የተከራካሪዎችን መብት ባከበረ መልኩ እንዴት ዘገባዎችን መስራት እንዳለባቸው ግንዛቤ የሚፈጥር ነው ያሉት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ ፍርድ ቤቶች የሚሰጧቸው ውሳኔዎች በአንድ ሀገር የኢኮኖሚ ፣ የማህበራዊና የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ ያላቸው ጉልህ አስተዋጽኦ በምን አግባብ ለህብረተሰቡ ተደራሽ መሆን እንዳለባቸው ግንዛቤ የሚፈጥር ነው ብለዋል። በፍርድ ቤት ጉዳዮች አዘጋገብ ላይ ስልጠናውን የሰጡት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሲኒየር ዳኛና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ወይዘሮ ቅድስት ገ/ህይወት ሲሆኑ፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የስትራቴጂክ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ፍሬው ታደሰ በበኩላቸው፣ የክልሉን ፍርድ ቤቶች የትላንት ነባራዊ ሁኔታ፣ አሁን ላይ ያሉበትን ስር ነቀል የለውጥና ማሻሻያ ሂደት እንዲሁም ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ስልጠናውን ለተከታተሉ የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች ገለጻ አድርገዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *