ባህርዳር፣ ሰኔ 02/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)
በክልሉ ፍርድ ቤቶች በብዛት በሚቀርቡ ጉዳዮች ላይ ዳኞች ተቀራራቢ መረዳት እንዲኖራቸው የሚያግዝ እና የዳኞችን ጥራት ያለው ውሳኔ ሰጭነት የሚያጎለብተው የዳኞች ሙያዊ የህግ ውይይት በሁሉም የክልሉ ፍርድ ቤቶች በመደበኛነት እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል።
ከ2018 በጀት ዓመት የፍርድ ቤቶች የመጀመሪያዎቹ የስራ ወራት ጀምሮ ያለማቋረጥ በመደበኛነት እየተካሄደ የሚገኘው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ሙያዊ የህግ ውይይት፣ ዛሬም 'በአጭርና በተፋጠነ ሁኔታ በሚወሰኑ ክርክሮች ላይ የሚፈጸም ስነ-ስርዓት' በሚል ርዕስ መደበኛ ውይይታቸውን አካሂደዋል።
በርዕሱ ላይ የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኛ፣ ክቡር ዳኛ አቶ ፈንታ ታረቀኝ ሲሆኑ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኞችም በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ለሌሎች ተሳታፊዎች ተጨማሪ ሙያዊ ግብዓት ሊሆን የሚችል ሀሳብና አስተያይታቸውን ሰጠዋል።
በ2018 በጀት ዓመት ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በሰው ሀይል አቅም ግንባታ ከያዛቸው እና በትኩረት እየሰራባቸው ካሉ ጉዳዮች አንዱ የሆነው የዳኞች ሙያዊ የህግ ውይይት በየደረጃው ባሉ የክልሉ ፍርድ ቤቶች ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ ውይይቱ ፣ ለዳኞች ተጨማሪ ሙያዊ አቅም መፍጠር ችሏል።









