ባህር ዳር፣ ግንቦት 28/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)
ተከሳሾች 1ኛ. ዳኘው ግስሜ ሞገስ እና 2ኛ. መምህር ሙላት አስማማው ገብሬ የሌላውን ሰው መብት ወይም ጥቅም ለመጉዳት ወይም ለራሳቸው ወይም ሌላ ሰው ተገቢ ያልሆነ መብት ወይም ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት በማሰብ አቶ መልካሙ አዛገ የተባለ ግለሰብ በካርታ ቁጥር 272/960/2008 በቀን 3/3/2008 ዓ/ም የተሠጠውን ስፋቱ 187.5ካ/ሜ የሆነውን ቤትና ቦታ በ2015ዓ/ም መጋቢት ወር ላይ የግንባታ ማሻሻያ ፍቃድ አውጥቶ በመስራት ላይ እያለ 2ኛ ተከሳሽ መ/ር ሙላት አስማማው ከቤታቸው ድረስ በመሄድ በግቢው የሚገኘውን 62.5ካ/ሜ ትርፍ የመንግስት ቦታ ማዘጋጃ ቤት መዝገብ ቤት ሆኖ ከሚሰራው ጓደኛዬ 1ኛ ተከሳሽ ጋር በመሆን በህጋዊ ቦታችሁ አካትትላችኃለሁ በማለት 60,000 ብር ከአቶ መልካሙ አዛገ ባለቤት ከሆኑት ከወ/ሮ አስጣሉ መለሰ በመቀበል ከ1ኛ ተከሳሽ ጋር በመሆን የአቶ መልካሙ አዛገ ትክክለኛ ካርታ ከከተማ አስተዳደሩ ከተማና መሰረተ ልማት ጽ/ቤት መዝገብ ቤት እዲጠፋ በማድረግ በምትኩ 62.5ካ/ሜ ትርፍ የሆነውን የመንግሥት ቦታ ወደ መልካሙ አዛገ ቦታ እንደተካተተ በማስመሰል 250ካ/ሜ ቦታ የሚል በ2009ዓ/ም የተዘጋጀ አስመስለው ሀሰተኛ ካርታ በማዘጋጀት በመንግስት ጥቅም ላይ ጉዳት ያደረሱ በመሆኑ የወንጀል ህግ አንቀጽ 33 እና የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 3፣23(2) እና አንቀጽ 24(2) ስር የተመለከቱትን ድንጋጌዎች በመተላለፍ መንግስታዊ ሰነዶችን አሰመስሎ ማዘጋጀትና ወደ ሀሰት መለወጥ እንዲሁም መንግስታዊ ሰነዶችን በማጥፋት የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል በሚል በሰሜን/ጎ/ዞን/ ፍትህ መምሪያ ዐ/ህግ በኩል ሁለት ተደራራቢ ክሶች ተመስርቶባቸዋል፡፡
ተከሳሾች የወንጀል ድርጊቱን አልፈጸምነም ጥፋተኛ አይደለንም በማለት ክደው ተከራክረዋል፡፡
ከሳሽ ዐ/ህግ ተከሳሾች የወንጀል ድርጊቱን የፈጸሙ መሆኑን ያስረዱልኛል ያላቸውን ማስረጃዎች ያቀረበ ሲሆን፣ ተከሳሾች በበኩላቸው በፍርድ ቤቱ እንዲከላከሉ የተሰጠውን ብይን ተከትለው የመከላለከያ ማስረጃዎችን አቅርበው አሰምተዋል፡፡
ጉዳዮን ሲከታተል የቆየው የሰሜን ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረቡትን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ከመረመረ በኃላ ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
ግንቦት 21/2018 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሾችን ያስተምራል ሌሎችን ያስጠነቅቃል በማለት ሁለቱም ተከሳሾች በ17ዓመት ፅኑ እስራት እና በ10,000 (አስር ሽህ ብር ) የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ መወሰኑን የሰሜን ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የህዝብ ግንኙነት ዘግቧል።
