ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

በባሕል ፍርድ ቤቶች የአሰራር ሂደት እና ማስተግበሪያ ሕጎች ላይ በሰሜን ሸዋ ዞን ለሚገኙ የባሕል ፍርድ ቤት ሽማግሌዎች ስልጠና ተሰጠ

በባሕል ፍርድ ቤቶች የአሰራር ሂደት እና ማስተግበሪያ ሕጎች ላይ በሰሜን ሸዋ ዞን ለሚገኙ የባሕል ፍርድ ቤት ሽማግሌዎች ስልጠና ተሰጠ

ደብረብርሃን ፣ግንቦት 23/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ 2018 በጀት ዓመት በልዩ ትኩረት ከያዛቸው እቅዶች ውስጥ የክልሉን የባሕል ፍርድ ቤቶች በሁሉም የክልሉ ቀበሌዎች ተግባራዊ ማድረግ ይገኝበታል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በእቅዱ አግባብ በጥናት የለያቸውን 15 ባሕላዊ ያለመግባባት መፍቻ ስርዓቶች የክልሉ የባሕል ፍርድ ቤቶች አድርጎ እውቅና የሰጠ እና ስራ ያስጀመረ ሲሆን፣ ከ 1 ሺህ በሚበልጡ የክልሉ ቀበሌዎች የባሕል ፍርድ ቤቶች ሽማግሌዎች እና ጽሀፊዎችን ማስመረጥ ችሏል።

በየቀሌዎቹ ለሚገኙ የባሕል ፍርድ ቤቶች ሽማግሌዎች አስፈላጊውን የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት ስራቸውን በይፋ እንዲጀምሩ እያደረገ ያለው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፣ በደቡብ ወሎ፣ በማእከላዊ ጎንደር፣ በባህርዳር እና አካባቢዋ ለሚገኙ የባሕል ፍርድ ቤቶች ሽማግሌዎች አስፈላጊውን የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት ስራቸውን በይፋ እንዲጀምሩ ማድረግ ችሏል።

በሰሜን ሸዋ ዞን ለሚገኙ የባሕል ፍርድ ቤቶች ሽማግሌዎችም ተመሳሳይ የስራ ማስጀመሪያ እና የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት ስራቸውን በይፋ እንዲጀምሩ የሚያስችል መድረክ ተካሂዷል።

ግንቦት 22/2018 ዓ.ም የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው እና ሌሎች የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በተገኙበት የስራ ማስጀመሪያ መድረክ የተካሄደ ሲሆን በእለቱ ሞዴል የባሕል ፍርድ ቤቶች ተከፍተው ስራቸውን በይፋ የጀመሩ ሲሆን፣ በዛሬው እለት ደግሞ ሽማግሌዎችና ጽሀፊዎች ስራቸውን እንዴት ማከናወን እንደሚችሉ የአቅም ግንባታ ስልጠና የተሰጣቸው ሲሆን፣ የባሕል ፍርድ ቤቶቹ በሚመሩባቸው አዋጆችና መመሪያዎች ላይም በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ ተችሏል።

የአቅም ግንባታ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው በባህል ፍርድ ቤቶች ጥናት፣ በባሕል ፍርድ ቤቱ አዋጅና መመሪያዎች ላይ የተሰጠ ሲሆን፣ ስልጠናውን የሰጡት በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የባሕል ፍርድ ቤቶች አማካሪ ምክር ቤት ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ይማም ሰይድና ክቡር ዳኛ ትዕዛዙ ጌታቸው ናቸው።

ስልጠናው የባሕል ፍርድ ቤት ሽማግሌዎችና ጸሀፊዎቹ ስራቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የሚያስችል ሲሆን፣ ሽማግሌዎቹ ያሏቸውን ጥያቄዎች አንስተው ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጦባቸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *