ደብረብርሃን ፣ ግንቦት 22/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የባሕል ፍርድ ቤቶችን ስራ በማስጀመር ላይ መሆኑ ይታወቃል።
በጥናት ለለያቸው 15 ባሕላዊ ያለመግባባት መፍቻ ስርዓቶችን የክልሉ የባሕል ፍርድ ቤቶች አድርጎ እውቅና የሰጠው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፣ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የባሕል ፍርድ ቤቶች ሽማግሌዎችን እና ጸሀፊዎችን ያስመረጠ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት ለተመረጡ ሽማግሌዎች እና ጽሀፊዎች አስፈላጊውን የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት ስራ በማስጀመር ላይ ይገኛል።
ከወራት በፊት በባህርዳር እና አካባቢዋ፣ ደሴ እና ማዕከላዊ ጎንደር ለሚገኙ የባሕል ፍርድ ቤት ሽማግሌዎች ስልጠና በመስጠት እና ሞዴል የባሕል ፍርድ ቤቶችን በይፋ በማስመረቅ ስራ ያስጀመረው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፣ በዛሬው እለትም በሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙ የባሕል ፍርድ ቤቶች ስራ ማስጀመሪያ አካል የሆነውን የልቼ ቀበሌ ሞዴል የባሕል ፍርድ ቤት መርቆ በመክፈት በይፋ ስራ አስጀምሯል።
ሞዴል የባሕል ፍርድ ቤቶችን ከፍትሕ ሚኒስትር ሚኒስቴር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ/ር) እና ሌሎች የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ጋር በመሆን መርቀው የከፈቱት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው ሲሆኑ፣ ክቡር ፕሬዝዳንቱ በምረቃው ወቅት የባህል ፍርድ ቤት ዳኞች በባህል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 298/2017 ላይ የተመለከቱ መርሆዎችን በመከተል በተለይም ሰብአዊ መብቶችን በማክበር፣ የህጻናት እና ሴቶችን መብት በመጠበቅ፣ በባህል ህጎች መሰረት በነጻነት ስራቸውን መስራት የሚገባቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የማዕከል ግንባታ በማከናወን እና ስራ ለማስጀመር የሚያስችሉ ድጋፎችን ላደረጉት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።





