ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

“የባሕል ፍርድ ቤቶች የዜጎችን ፍትሕ የማግኘት መብት የሚያረጋግጡ እና ፍትሕን ተደራሽ የማድረግ አቅም ያላቸው ናቸው” ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው- የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት

“የባሕል ፍርድ ቤቶች የዜጎችን ፍትሕ የማግኘት መብት የሚያረጋግጡ እና ፍትሕን ተደራሽ የማድረግ አቅም ያላቸው ናቸው” ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው- የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት

ደብረብርሃን ፣ ግንቦት 22/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በክልሉ የባሕል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 298/2017 መሰረት እዉቅና ለተሰጣቸው የባሕል ፍርድ ቤቶች የስልጠና እና አቅም ግንባታ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል። በዛሬው እለትም ከፌደራል ፍትሕ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በተለያየ ቀበሌ ለሚገኙ የባሕል ፍርድ ቤቶች ይፋዊ ስራ ማስጀመሪያ እና የአቅም ግንባታ ስልጠና መድረክ ተካሂዷል።

የስልጠና መድረኩን የከፈቱት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው ፣ የባሕል ፍርድ ቤቶችን በሙሉ አቅም ስራ ለማስጀመር ማስተግበሪያ ፍኖተ ካርታ፣ ወጥ የሆነ ስልጠና ለመስጠት የሚያስችል የስልጠና ማንዋል እና የኮሚኒኬሽን ስትራቴጂ በመንደፍ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ በሚገኙ 1170 ቀበሌዎች ላይ የባሕል ፍርድ ቤት ዳኞች ምርጫ የተደረገ መሆኑን የገለጹት ክቡር ፕሬዘዳንቱ፣ ሴቶች አለመግባባትን ለመፍታት ያላቸውን ሚና በሚያሳይ መልኩ ከ400 የሚበልጡ ሴት ሽማግሌዎች መመረጣቸውን ገልጸዋል።

የባሕል ፍርድ ቤቶች ፍትሕን ተደራሽ የሚያደርጉ እና ወጪ ቆጣቢ ፣ እንዲሁም ቀለል ያለ እና ማህበረሰቡ የሚያውቀውን ስርዓት የሚከተሉ በመሆኑ እውነትን ለማውጣት እና የሻከሩ ግንኙነቶችን የመጠገን አቅም ያላቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።

የባሕል ፍርድ ቤቶችን በማደራጀት እና በማጠናከር ሁላችንም የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል ያሉት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ የባሕል ፍርድ ቤቶች ማዕከላት ግንባታ እና ለባህል ፍርድ ቤት ዳኞች የአቅም ግንባት ስልጠና ለመስጠት ድጋፍ ያደረጉ አካላትን አመስግነዋል።

በእለቱ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የፍትሕ ሚኒስትር ሚኒስቴር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ፍትሕ ሚኒስትር ባሕላዊ የፍትሕ ማግኛ ዘዴዎችን ለማስፋፋት እቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል።

ማህበረሰባችን ለብዙ ዘመናት የሚጠቀምባቸው የዳበሩ የፍትሕ መስጫ ተቋማት ያሉት መሆኑን የገለጹት ሚኒስቴር ዴኤታው፣ 43 ከመቶ የሚሆኑት አለመግባባቶች በባሕላዊ አለመግባባት መፍቻ ስርዓቶች የሚፈቱ መሆኑን በፍትሕ ሚኒስትር በተደረገ ጥናት መረጋገጡን ገልጸዋል።

ለባሕል ፍርድ ቤቶች እውቅና መሰጠቱ የባሕል ፍርድ ቤቶች የሚሰጡት ውሳኔ እንዲፈጸም የሚያስችል እና የማህበረሰቡ አሴት እንዲጎለብት የሚያግዝ መሆኑንም አንስተዋል።

ፍትሕ ሚኒስትር ሞዴል ሕግ ከማዘጋጀት ጀምሮ ስልጠና በመስጠት እና ለባሕል ፍርድ ቤት ማዕከላት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ኤርሚያስ፣ በዛሬው መድረክ መገኘታቸውም የዚህ ድጋፍ አካል መሆኑን ገልጸዋል። በመድረኩ የተገኙት የዞኑ ከፍተኛ ባለስልጣናት በበኩላቸው፣ የባሕል ፍርድ ቤቶችን ለማደራጀት ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሄደበትን እርቀት አመስግነው፣ ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *