ደብረብርሃን ፣ ግንቦት 21/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የክልሉን የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ያለው፣ ቀልጣፋ፣ ዘመናዊ፣ ተገማች፣ ጊዜ እና ወጪ ቆጣቢ በማድረግ፣ ፍርድ ቤቶች የህዝብ አመኔታን ያተረፉ እንዲሆኑ እየሰራ ይገኛል።
በጠቅላይ ፍርድ ቤት የተጀመረውን ዘመናዊ የዳኝነት መስጫ የጂዲታላይዜሽን ስራ፣ ምቹ የስራ ከባቢ እና በግልጽ ችሎት የመዳኘት ህገ መንግስታዊ መብት የሚረጋገጥባቸው ፍርድ ቤቶችን በዞን እና ወረዳ ፍርድ ቤቶች ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ የሚገኘው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በክልሉ በሚገኙ 14 የዞን ከፍተኛ ፍርድቤቶች የስማርት ችሎት አገልግሎት መጀመሩ የሚታወስ ነው።
በዛሬው እለትም፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደውን እና የኢፌዲሪ ፍትህ ሚኒስትር ሚኒስቴር ዴኤታ ክቡር ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ/ር) ጨምሮ፣ የፌደራል እና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመገኘት ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፣ በጉብኝታቸው ስማርት ችሎቶችን፣ የኢፋይሊንግ ትግበራ፣ ዳኝነት በግልጽ የሚሰጥባቸውን የችሎት አዳራሾች ጨምሮ ሌሎች የከፍተኛ የፍርድ ቤቱን አገልግሎቶች ተመልክተዋል።
ፍርድ ቤቶችን ጠንካራ ማድረግ የአንድ ዲሞክራሲያዊ ሀገር ግንባታ መሰረት መሆኑን በጉብኝቱ ወቅት የገለጹት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዘዳንት ክቡር አቶ አለም አንተ አግደው፣ የለውጥ ስራዎችን ወደ ወረዳ ፍርድ ቤት ለማድረስ በስፋት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በጉብኝቱ የተገኙት የፌደራል እና የክልል አመራሮች ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በሁሉም የክልሉ ፍርድ ቤቶች ዘመናዊ የዳኝነት አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የሰራቸውን ስራዎች አድንቀዋል።








