ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የወንጀል መከላከልና ዕጽ ቁጥጥር የኢትዮጵያ ቢሮ ሀላፊ እና የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን ውይይት አካሄዱ

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የወንጀል መከላከልና ዕጽ ቁጥጥር የኢትዮጵያ ቢሮ ሀላፊ እና የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን ውይይት አካሄዱ

ባህርዳር፣ ግንቦት 12/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በክልሉ የዳኝነት እና የፍትሕ ስርዓት ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገቡ ያሉ የለውጥና የማሸሻያ ስራዎችን በዘላቂነት ለማስቀጠል ከተለያዩ አጋርና ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር መስራት የሚያስችለውን ውይይት እና ስምምነት በማድረግ ላይ ይገኛል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በዛሬው እለትም ትኩረቱን በወንጀል መከላከል እና እጽ ቁጥጥር ላይ አድርጎ ከሚሰራው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቢሮ ሀላፊዎች ጋር በወንጀል መከላከል እና ሌሎች ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የዳኝነት እና የፍትሕ ስርዓቱን በዘላቂነት ለማሻሻል እየተገበራቸው ያሉ አሰራሮችን በስፋት አጠናክሮ ማስቀጠል በሚቻልበት አግባብ ተወያይቷል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የወንጀል መከላከልና እጽ ቁጥጥር የኢትዮጵያ ቢሮ ሀላፊ አቶ አብርሃም አያሌውና የልኡካን ቡድናቸውን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው ያነጋገሩት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የክልሉን የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት የትብብር መድረክ በበላይነት እንዲመራ በአዋጅ ስልጣን እንደተሰጠው ጠቅሰው፣ ቢሮው የተደራጁ ወንጀሎችን በመከላከል፣ በክልሉ ያለውን የዳኝነት እና የፍትሕ ተደራሽነት በትክክለኛ መለኪያ እና በጥናት ለመለየት፣ በጥናትና ምርምር፣ በአቅም ግንባታ፣ የሁሉንም የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማት መረጃ በአንድ ማእከል ለማደራጀት በምናደርገው ጥረት አብሮን የሚሰራ ይሆናል ብለዋል።

በጠቅላይ ፍርድ ቤት እና በዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ደረጃ የተጀመሩ የዘመናዊ የዳኝነት አገልግሎት መስጫዎችን ወረዳዎች ድረስ ተደራሽ በማድረግ ለፍትሕ ተደራሽነት ከቢሮው ጋር በትብብር እንሰራለን ያሉት ክቡር ፕሬዝዳንቱ፣ ክልሉን ለማገዝ የመጡትን የቢሮው ሀላፊዎች አመስግነዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የወንጀል መከላከልና የእጽ ቁጥጥር የኢትዮጵያ ቢሮ ሀላፊ አቶ አብርሃም አያሌው በበኩላቸው፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዳኝነት እና በፍትሕ ስርዓቱ መሻሻል ላይ እያደረገ ያለውን የጎላ አስተዋጽኦ ማየት መቻላቸውን ጠቅሰው፣ የተጀመሩ የለውጥና የማሻሻያ ስራዎችን በሚችሉት ሁሉ ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *