ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

ከተለያዩ የህግ ተቋማት ለተወጣጡ ባለሙያዎች በካፒታል ገበያ አሰራርና ህጎች  ላይ ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቀቀ

ከተለያዩ የህግ ተቋማት ለተወጣጡ ባለሙያዎች በካፒታል ገበያ አሰራርና ህጎች  ላይ ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቀቀ

ባህርዳር፣ ግንቦት 01/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጡን ከተለመደ አሰራር በማላቀቅ ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ፣ ተደራሽ፣ ተገማች እና አመኔታን ያተረፈ ለማድረግ በሁሉ አቀፍ የለውጥና ማሻሻያ ሂደት ላይ ይገኛል።

ምቹ የስራ ከባቢ በመፍጠር እና የዘመናዊ ዳኝነት አገልግሎት መስጫ  መሰረተ ልማቶችን በሁሉም የክልሉ ፍርድ ቤቶች በመገንባት ላይ የሚገኘው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፣ የተቋም ግንባታውን ሙሉ ለማድረግ የሚዘረጉ መሰረተ ልማቶችን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል የሚችል አመራር፣ ዳኛ እና ሰራተኛ ለመፍጠር የአጭር እና የረጅም ጊዜ የስልጠና አማራጮችን በመጠቀም አቅማቸውን በመገንባት ላይ ነው።

የዚህ አቅም ግንባታ ፈጠራ አካል የሆነ የትብብር ስምምነት ከኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ጋር የተፈራረመው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፣ የክልሉ ዳኞች፣ አቃቢያነ ህጎችና ሌሎች የሕግ አካላት ለሀገራችን አዲስ በሆነው የካፒታል ገበያ አሰራሮች እና የህግ ማእቀፎች ላይ ከሀሙስ ሚያዚያ 29/ 2018 ዓ.ም እስከ ቅዳሜ ግንቦት 01/2018 ዓ. ም ለሶስት ቀናት የቆየ ስልጠና ሰጧል።

የዳኝነት እና የፍትህ አካላት በካፒታል ገበያ ዙሪያ የሚነሱ ክርክሮችን ለመፍታት ተመሳሳይ የህግ አተረጓጎም እንዲኖር ለማስቻል በህግ ማዕቀፉ ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ታሳቢ በማድረግ የተሰጠው ስልጠናው ፣ እንደ ሀገር እየተዋወቀ የሚገኘው የካፒታል ገበያ ስርዓት በህብረተሰቡ፣ በባለአክሲዎኖች፣ በአልሚዎች እና በሌሎች ባለድርሻ አካላት አመኔታን በማትረፍ ለሀገር ምጣኔ ሀብታዊ እድገት የበኩሉን ድርሻ እንዲያበረክት ማስቻል ነው።

ስልጠናው፣ ጥልቀት ያለው ካፒታል ገበያ የሕግ ማእቀፍ፣ የጋርዮሽ ኢንቨስትመንት ፈንድ፣ የኢንቨስተሮች ጥበቃ፣ የተከለከሉ ተግባራት እና በገበያው ሊከተሉት ስለሚገባው ስነምግባር እንዲሁም በአክሲዮን ግብይት ሂደቶች እና በሌሎች ርእሰ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን አድርጎ ሲሰጥ የቆየ ሲሆን፣በዘርፉ የካበተ ልምድ ባላቸው የአስተዳደራዊ ፍርድ ቤቱ ዳኞች፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ ጠበቆችና ሌሎች የህግ ባለሙያዎች ተሰጧል።

ስልጠናውን የወሰዱ፣ ከአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ከክልሉ የፍትሕና ህግ ኢኒስቲትዩት፣ ከአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ እና ከርእሰ መስተዳደር ጽ/ቤት የተወጣጡ ዳኞች፣ አቃቢያነ ህጎች እና የህግ ባለሙያዎች፣ ካፒታል ገበያን በተመለከቱ  መመሪያዎች ፣ አዋጆች እና አሰራሮች ላይ ጥልቅ ግንዛቤ እንዳገኙ  ተናግረዋል።

የኢትዮጲያ የካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት  ከክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጋር በመተባበር  የአቅም ግንባታ ስልጠናውን በቋሚነት መስጠት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሙ ይታወሳል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *