ባህርዳር፣ ሚያዚያ 29/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የክልሉን የዳኝነት እና የፍትሕ አገልግሎት በሚታይ መልኩ ለማሻሻል ተጨባጭ የለውጥ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል።
በዘመናዊ የዳኝነት አገልግሎት መስጫ መሰረተ ልማት ዝርጋታ እና በሁሉ አቀፍ ዘላቂ የተቋም ግንባታ ላይ የሚገኘው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፣ የሁሉም መሰረቱ ብቃት ያለው አመራር፣ ዳኛ እና ሰራተኛ ነው በሚል መርህ፣ በየደረጃው የሚገኙ ፍርድ ቤቶች አመራሮችን፣ ዳኞችን እና ሰራተኞችን አቅም ለማሳደግ እየሰራ ይገኛል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በዛሬው እለት ከኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ጋር የተፈራረመው የመግባቢያ ሰነድ ፊርማ ስነስርዓት፣ የዚህ አቅም ግንባታ ፈጠራ ፕሮግራም አካል ሲሆን፤ ዳኞች፣ አቃቢያነ ህጎች እና ሌሎች የህግ አካላት ከካፒታል ገበያ ጋር የተገናኙ ሀገር እና አለምአቀፍ ህጎች ላይ በቂ እውቀት እንዲኖራቸው የሚያግዝ ነው።
የስምምነት ሰነዱን፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው እና የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ሰብሳቢ ዳኛ አቶ አብነት ዘርፉ ተፈራርመዋል።
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ካሁን በፊት በሰሩባቸው ከፍተኛ ተቋማት ያካበቱት ልምድ፣ አርቆ አሳቢነት እና አዳዲስ ሀሳቦችን ለማስረጽ ያላቸው ቁርጠኝነት ለሀገራችን አዲስ በሆነው የካፒታል ገበያ ላይ የክልሉ ዳኞች፣ አቃቢያነ ህጎችና ሌሎች የህግ ባለሙያዎች በቂ እውቀት እንዲኖራቸው ያላቸው ብርቱ ፍላጎት ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጋር በትብብር እንድንሰራ አድርጎናል ያሉት የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ሰብሳቢ ዳኛ አቶ አብነት ዘርፉ፣ ስምምነቱ የክልሉ የህግ አካላት ሀገር አቀፍ እና አለምአቀፍ የካፒታል ገበያ ህጎችን ጠንቅቀው እንዲያውቁ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
የካፒታል ገበያ ሀብት ከአንዱ ክልል ወደ ሌላው ክልል፣ ከአንድ ሀገር ወደ ሌላ ሀገር በቀላሉ እንዲንቀሳቀስ ያስችላል ያሉት አቶ አብነት፣ ስምምነቱ ይሄንን ሀብት በአግባቡ የሚመራ የሰው ሀይል ለማፍራት ያስችላል ብለዋል።
አብረናችሁ እንድንሰራ እድሉን ስለጣችሁን እናመሰግናለን ያሉት ሰብሳቢ ዳኛው፣ ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጋር ያደረግነው ስምምነት እና በስምምነቱ መሰረት ለክልሉ ዳኞች፣ አቃቢያነ ህጎችና ሌሎች የህግ አካላት የምንሰጠው የአቅም ግንባታ ስልጠና ለሌሎች ክልሎችም አርአያ የሚሆን ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤታችን ስምምነቱን ከኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ጋር ያደረገው የክልሉን ዳኞችና የህግ ባለሙያዎች በካፒታል ገበያ እና ሌሎች ህጎች ላይ አቅማቸውን ለመገንባት ነው ያሉት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ በምጣኔ ሀብት እና በዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ላለች ሀገር፣ ስምምነቱ በእነዚህ መስኮች ላይ የተጀመሩ የማሻሻያ ስራዎችን መሬት ለማውረድ የሚያስችል ነው ብለዋል።
የህግ ተቋማት ነጻና ገለልተኛ ሆነው በመስራት የባላክሲዎኖች እና ባለሀብቶችን መብት በማስጠበቅ የካፒታል ገበያው ለሀገር ምጣኔ ሀብት እድገት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ዘርፉን የተመለከቱ ሀገር እና አለምአቀፍ ህጎችን አውቆ መገኘት ያስፈልጋል ያሉት ክቡር ፕሬዝዳንቱ፣ ሁለቱ ተቋማት የህግ ባለሙያዎችን አቅም ለማጎልበት ያካሄዱት የትብብር ስምምነት በተጀመሩ የለውጥና የማሻሻያ ስራዎች ላይ እንደ ክልል እና እንደ ሀገር የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት የሚያስችላቸው ነው ብለዋል።
ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው ከፊርማ ስነስርዓቱ በኋላ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤቱ ለክልሉ የዳኝነት እና የፍትህ አካላት የሚሰጠውን ስልጠና በይፋ አስጀምረዋል።
