ባህር ዳር፣ ሚያዚያ 20/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነጻ፣ ገለልተኛ፣ ተደራሽ፣ ፈጣን እና ወጪ ቆጣቢ የሆነ ውጤታማ የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ የተለያዩ የአሰራር ስርዓቶችን በመተግበር ላይ ይገኛል።
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነጻነቱን ባከበረ መንገድ የፍትህ ስርዓቱን ውጤታማ ለማድረግ በፍትሕ ስርዓቱ ውስጥ ሚና ካላቸው ከተለያዩ አካላት ጋር በጋራ በመስራት ላይ ይገኛል። በዛሬው እለትም የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዘዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው በህግ ከተቋቋመው የክልሉ የጠበቆች ማህበር አመራሮች ጋር ውይይት አካሂደዋል።
በውይይቱ፣ ጠበቆች የፍትሕ አካሉ አጋር እና በፍትሕ አገልግሎት ውጤታማነት ላይ ትልቅ ድርሻ ያላቸው ናቸው ያሉት ክቡር ፕሬዘዳንቱ፣ ጠበቆች የፍትህ ተደራሽነትን ማረጋገጥ እና የወከሏቸውን ዜጎች መብት ማስከበር ዋና ስራቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ጠበቆች በፍትሕ ተቋማት የሪፎርም ስራዎች፣ በዳኝነት እና የፍትሕ አካላት የትብብር መድረክ፣ እንዲሁም በነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎት በመስጠት ትልቅ አስተዋጾ የሚኖራቸው መሆኑን አንስተዋል።
በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በህግ አስገዳጅ ሆኖ እና እራሱን እንዲያስተዳድር ተደርጎ የተቋቋመው የጠበቆች ማህበር ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራቸው ከሚገባቸው ጉዳዮች ውስጥ የጠበቆችን የሙያ ብቃት እና ስነ ምግባር ማሳደግ ግንባር ቀደሙ መሆኑን ክቡር አቶ አለምአንተ አንስተዋል። ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተጠሪ ከሆነው የክልሉ የፍትሕ እና የህግ ምርምር ኢንስቲቲዩት እና በክልሉ ከሚገኙ ዩንቨርሲቲዎች ጋር በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የማህበሩ አመራሮችም ማህበሩ አዲስ እንደመሆኑ ብዙ ኃላፊነቶች የሚኖሩባቸው ቢሆንም የተሰጣቸውን ስልጣን እና ኃላፊነት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በሀገር አቀፍ ደረጃ ተምሳሌት የሆነ ተቋም እንዲሆን ለማስቻል መስራት የሚገባ ስለመሆኑ ክቡር አቶ አለም አንተ አግደው አሳስበዋል።
በዉይይቱ የተሳተፋት የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሀኑ ጎሽም በበኩላቸው፣ የጠበቆችን አዋጅ በ2017 ዓ/ም ከጠቅላይ ፍርድ ቤት ጋር በመሆን ማውጣት የተቻለ መሆኑን አውስተው፣ የጠበቆች ማህበር ከፍርድ ቤት እና ከፍትህ ቢሮ ጋር በመተባበር የፍትሕ ስርዓቱን ውጤታማ ለማድረግ ሊሰራ የሚገባው መሆኑን ገልጸዋል።
የጠበቆች ማህበር ፕሬዘዳንት አቶ ሰለሞን ጎራው በበኩላቸው፣ የጠበቆች ማህበር በህግ በአስገዳጅ ሁኔታ እንዲቋቋም መደረጉ መልካም መሆኑን ገልጸው፣ የሙያ ስታንዳርድ እና ስነ-ምግባር በዋነኝነት የሚሰሩበት ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ጠበቆች የፍርድ ቤቶችን የዘመናዊ ዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ የለውጥ ሂደቶች ተከትለው እንዲሄዱ ማድረግ የሚገባ መሆኑን አንስተው፣ አዋጅ እንዲወጣ በማድረግም ሆነ የአመራር ምርጫ ሲካሄድ ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።
በውይይቱ የክልሉ የፍትሕ እና ህግ ኢንስቲቲዩት ፕሬዘዳንት ዶክተር ደሴ ጥላሁን፣የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አመራሮች እና የጠበቆች ማህበር አመራሮች ተሳትፈዋል።
