ባህርዳር ፣ ህዳር 20/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ቀበሌዎች የባህል ፍርድ ቤቶችን ስራ በማስጀመር ላይ ይገኛል።
15 ባህላዊ የአለመግባባት መፍቻ ዘዴዎችን የክልሉ ባህል ፍርድ ቤቶች አድርጎ እውቅና የሰጠው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፣ 1149 በሚሆኑ ቀበሌዎች ውስጥ የባህል ፍርድ ቤት ሽማግሌዎችን በአካባቢው ህብረተሰብ ጠቋሚ እና መራጭነት ማስመረጥ ችሏል።
እስካሁን ምርጫ በተካሄደባቸው ቀበሌዎች 5494 ሽማግሌዎች የተመረጡ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ 437 የሚሆኑት ሴቶች ናቸው።
የተመረጡ የባህል ፍርድ ቤቶች ሽማግሌዎችን ስራ ለማስጀመር የአቅም ግንባታ ስልጠና መሰጠት ተጀምሯል።
በዛሬው እለት ለባህርዳር ከተማ የባህል ፍርድ ቤት ሽማግሌዎች በመስጠት የተጀመረው ስልጠናው፣ በቀጣይም በማእከልነት በተመረጡ የተለያዩ የክልሉ ከተሞች ስልጠናው የሚሰጥ ይሆናል።
በስልጠና ማስጀመሪያ መድረኩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ ምንም እንኳን አለመግባባትን በባህላዊ ዘዴዎች መፍታት ህገ መንግስታዊ መብት ቢሆንም፣ የአለመግባባት መፍቻ ዘዴዎችን እውቅና መስጠት እና ድጋፍ ከማድረግ አንጻር ተግባራዊ ሳይደረግ ቆይቷል ብለዋል።
የባህል ፍርድ ቤቶችን አማራጭ ያለመግባቢያ መፍቻ ዘዴዎች አድርጎ መጠቀም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው ያሉት ክቡር ፕሬዝዳንቱ፣ ፍትህን ተደራሽ ለማድረግ፣ ቁርሾን እና ግጭትን በዘላቂነት ለመፍታት እና እውነትን በቀላሉ ለማውጣት ያግዛል ብለዋል።
የክልሉ ማህበረሰብ አለመግባባቶችን የሚፈታበት የዳበረ ልምድ እና ቱባ ባህል አለው ያሉት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በባህሉ ላይ የጨመረው አዲስ ነገር እንደሌለ ተናግረው፣ እያደረገ ያለው እውቅና መስጠት እና የህግ ድጋፍ ማድረግ ነው ብለዋል።
በአቅም ግንባታ ስልጠና ማስጀመሪያው ላይ የተገኙት የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሀን (ዶ/ር)፣ የባሕል ፍርድ ቤት ከመደበኛው የዳኝነት እና የፍትህ አገልግሎት መስጫ ስርዓቶች ጋር በአማራጭነት በማቅረብ ህብረተሰቡ ከወጭ እና ከእንግልት ተላቆ በአቅራቢያው ባሉ ሽማግሌዎች ለችግሩ መፍትሄ እንዲያገኝ የተጀመረ የፍትህ ትራንስፎርሜሽን አካል ነው ብለዋል።
በዛሬው የአቅም ግንባታ ስልጠና ማስጀመሪያ መድረክ ፣የአማራ ክልል ባህል ፍርድ ቤቶች አማካሪ ምክር ቤት ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ይማም ሰይድ ፣ የባህል ፍርድ ቤቶችን በተመለከተ የተካሄደውን ጥናትና አጠቃላይ ሂደቱን ለባህል ፍርድ ቤት ሽማግሌዎች አቅርበዋል።