ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የፍትሕና የሕግ ኢንስቲትዩት ቦርድ የኢንስቲትዩቱን አዲስ የአደረጃጀትና መዋቅር ጥናት በማጽደቅ የተለያዩ ስትራቴጂክ ውሳኔዎችን አሳለፈ

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የፍትሕና የሕግ ኢንስቲትዩት ቦርድ የኢንስቲትዩቱን አዲስ የአደረጃጀትና መዋቅር ጥናት በማጽደቅ የተለያዩ ስትራቴጂክ ውሳኔዎችን አሳለፈ

ባህር ዳር ፤ ሚያዚያ 19/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የአማራ ክልል የዳኝነት እና የፍትህ ትራንስፎርሜሽን ስራዎች የህግና ፍትሕ አቅም ግንባታ፤ ጥናትና ምርምር፤ እና የፍትህና የህግ መረጃ የልህቀት ማዕከል ሆኖ በአዋጅ ቁጥር 299/2017 እንደገና የተቋቋመው የፍትሕና የሕግ ኢንስቲትዩት ሰፋፊ የለውጥ ስራዎችን እየሰራ ሲሆን፣ የኢንስቲትዩቱ ቦርድ አዲስ በተጠናው የኢንስቲትዩቱ የአደረጃጀትና መዋቅር እና ሌሎች ስትራቴጂክ ጉዳዮች ላይ በመወያየት ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

የኢንስቲትዩቱ የቦርድ ሰብሳቢ እና የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ ዓለምአንተ አግደው፣ ኢንስቲትዩቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሰራቸው ሰፋፊ የሪፎርም ስራዎች የክልሉን የዳኝነት እና የፍትህ ትራንስፎርሜሽን ሥራዎች ተቋማዊ አድርጎ ለማስቀጠል ሁነኛ አቅም መሆኑን አንስተው፣ የኢንስቲትዩቱ የሪፎርም ስራዎች የሆኑ ስትራቴጂክ ጉዳዮች ላይ በመወያየት ውሳኔ ማሳለፉን ገልፀዋል፡፡

የአማራ ክልል የፍትሕና የሕግ ኢንስቲትዩት ቦርድ 3ኛ መደበኛ ስብሰባውን ያካሄደ ሲሆን፣ የኢንስቲትዩቱን የ2018 በጀት ዓመት የ9 ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ገምግሟል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በበጀት ዓመቱ 9 ወራት በዕቅድ የያዛቸውን ስራዎች በውጤታማነት መፈፀሙን ገምግሟል፡፡ የተቋሙን የፋሲሊቲና መሰረተ-ልማት የሚያሻሽሉ እና ለቀጣይ የተቋም ግንባታ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ ስራዎች ተሰርተዋል፤ የዳኞችና የዐቃቤያነ-ህግ የቅድመ ስራ ስልጠናዎች በብቃት እየተመሩ መሆኑ፤ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ብቃትና ችግር-ፈቺነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎች መሰራታቸው፤ በዘርፉ ስትራቴጂክ አጋርነትን በማሻሻል ኢንስቲትዩቱ የዓለም አቀፉ የዳኞች ማሰልጠኛ ድርጅት (IOJT) አባል እንዲሆን መደረጉ እና ሰፋፊ የሪፎርም ስራዎች መጀመራቸውን ቦርዱ ገምግሟል፡፡

በቀጣይ ወራትም የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችሉ አቅጣጫዎች ተሰጥተዋል፡፡ ቦርዱ በኢንስቲትዩቱ በመገኘትም የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎችን ጎብኝቷል፡፡ በጉብኝቱም ከቦርድ አባላት በተጨማሪ የኢፌዴሪ ፍትህ ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኤርምያስ የማነ-ብርሃን እና የሚኒስቴር መ/ቤቱ ከፍተኛ ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡

ቦርዱ በዕለቱ በያዛቸው አጀንዳዎችም ከኢንስቲትዩቱ የሪፎርም ስራዎች መካከል የብራንዲንግ አካል የሆነውን የኢንስቲትዩቱን ሎጎ አፅድቋል፤ የኢንስቲትዩቱ የፍትህና ህግ ሥርዓት ማሻሻያ የፕሮጀከት ስራዎች ተቋማዊነት ላይ ቀጣይ የሚሰሩ ስራዎችን በግምገማ ለይቷል፤ በአዲስ የተጠናውን የኢንስቲትዩቱን የአደረጃጀትና መዋቅር ጥናት በቫሊዴሽን ወርክሾፕ ላይ የተገኙ ግብዓቶችን በማካተት እንዲፀድቅ አድርጓል፡፡

የኢንስቲትዩቱ የቦርድ አባላት የአደረጃጀትና መዋቅር ጥናቱን የሚያዳብሩ ጠቃሚ ጉዳዮችን ያነሱ ሲሆን፣ የኢንስቲትዩቱ የቦርድ ሰብሳቢ ክቡር ዓለምአንተ አግደው፣ የአደረጃጀትና መዋቅር ጥናቱ ኢንስቲትዩቱ በህግ የተሰጡትን ተልዕኮዎች በመተግበር ውጤት ለማምጣት የሚያስችለው መሆኑንና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የአደረጃጀትና መዋቅርን መቅረጽ ለተቋማት ውጤታማነት አንድ መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም በቦርዱ የጸደቀው አዲስ የአደረጃጀትና መዋቅር ጥናት የመተግበሪያ የድርጊት መርሃ-ግብር ተቀርፆለት ወደ ስራ እንዲገባ የስራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

በዚሁ የቦርዱ 3ኛ መደበኛ ስብሰባ የኢንስቲትዩቱ የ2019 በጀት ዓመት የመደበኛ እና የካፒታል በጀት ጥያቄና ማብራሪያዎች ላይ ተወያይቷል፡፡

የመደበኛና የካፒታል በጀት ጥያቄዎቹ ኢንስቲትዩቱ በህግ የተሰጡትን ተልዕኮዎች በብቃት ለመፈፀም የሚያስችሉ እና ቦርዱ በተለያየ ጊዜ ያስቀመጣቸውን ስትራቴጂክ ጉዳዮች በማካተት የተዘጋጁ መሆኑን በማረጋገጥ፤ የኢንስቲትዩቱ የካፒታል ፕሮጀክት በጀት ዝግጅት እና ጥያቄም የተቋሙን የመሰረተ-ልማትና የፋሲሊቲ ጥያቄዎች በዘላቂነት የሚመልስ እና የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ለኢንስቲትዩቱ በሰጠው የ5 ሄክታር መሬት ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ተቋም ለመገንባት የሚያስችል መሆኑ አስተያየት በመስጠት በአሰራሩ መሰረት ለክልሉ ገንዘብ ቢሮ እንዲቀርብ ቦርዱ ወስኗል፡፡

በተያያዘም በክልሉ የሚገኙ የህግ ትምህርት ቤቶች ኮንሶርቲየም የክልሉን የዳኝነት እና የፍትህ ስራዎች በማገዝ እየተሰሩ ባሉ ጉዳዮች እና የቀጣይ ትኩረት ነጥቦች ላይ ሃሳቦች ተሰጥተዋል፡፡

በአጠቃላይ የኢንስቲትዩቱ የቦርድ ሰብሳቢ እና የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር ዓለምአንተ አግደው ኢንስቲትዩቱ የጀመራቸው የሪፎርም ስራዎች ተቋሙ በትክክለኛ አቅጣጫ ላይ መሆኑን በማንሳት በቀሪ የበጀት ዓመቱ ጊዚያት ዕቅዶችን በላቀ ብቃት መፈፀም እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

photo_12_2026-04-28_09-31-17
photo_11_2026-04-28_09-31-17
photo_10_2026-04-28_09-31-17
photo_9_2026-04-28_09-31-17
photo_8_2026-04-28_09-31-17
photo_7_2026-04-28_09-31-17
photo_6_2026-04-28_09-31-17
photo_2_2026-04-28_09-31-17
photo_5_2026-04-28_09-31-17
photo_4_2026-04-28_09-31-17
photo_3_2026-04-28_09-31-17

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *