ባህርዳር ፣ሚያዚያ 17/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት)
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ በፍርድ ቤት መር አስማሚነት አተገባበር እና አፈጻጸም የሙከራ ትግበራ ላይ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ዳኞች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
የውይይቱን አስፈላጊነት በተመለከ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አገደው፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የክልሉን ፍርድ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ በማሻሻል ቀልጣፋ የዳኝነት አገልግሎት ለተገልጋዩ ለማቅረብ ያሉትን አማራጮች ሁሉ በመጠቀም ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
ከመደበኛው የፍርድ ቤት አገልግሎት በተጨማሪ፣ የባሕል ፍርድ ቤቶችን ጨምሮ፣ ሌሎች ያለመግባባት ዘዴዎችን ሁሉ በመጠቀም ለተገልጋዩ አመች የሆኑ አማራጭ የዳኝነት መስጫዎችን እየተገበርን እንገኛለን ያሉት ክቡር ፕሬዝደንቱ፣ ከእነዚህ ውስጥም ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ ፍርድ ቤቶች በሙከራ ደረጃ እየተተገበረ ያለው የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ተጠቃሽ መሆኑን ገልጸው፣ የውይይቱ አስፈላጊነትም በእስካሁኑ የትግበራ ሂደት የተለዩ መልካም አጋጣሚዎችን በማስቀጠል፣ ያጋጠሙ ችግሮችን ደግሞ በመለየት እና የመፍትሄ አማራጮችን በማስቀመጥ፣ የፍርድ ቤት መር አስማሚነትን በሙሉ አቅም ተግባራዊ ለማድረግ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ልዩ አማካሪ ወርቁ ያዜ (ረ/ፕ) ፣ "የፍርድ ቤት መር አስማሚነት የሙከራ ትግበራ በአማራ ክልል:- ጠንካራ ጎኖችና ውስንነቶች" በሚል ርእስ የውይይት መነሻ የዳሰሳ ጥናት አቅርበዋል።
ልዩ አማካሪው በዳሰሳ ጥናታቸው፣ ስለ ፍርድ ቤት መር አስማሚነት ምንነት፣ አስፈላጊነት እና ጠቀሜታ፣ የፍርድ ቤት መር አስማሚነት በክልሉ የተለያዩ ፍርድ ቤቶች በሙከራ ደረጃ መተግበር ከጀመረበት ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ በአተገባበሩ እና አፈጻጸሙ ላይ የተለዩ መልካም አጋጣሚዎችን እና ተግዳሮቶችን፣ እንዲሁም የቀጣይ ምክር ሀሳቦችን ለውይይት አቅርበዋል።
የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች ፣ በቀረበው የዳሰሳ ጥናት መነሻነት ሀሳብና አስተያይታቸውን ሰጠዋል።
ለላቀ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ከመደበኛው የፍርድ ቤት አገልግሎት በተጨማሪ አማራጭ ያለመግባባት መፍቻ ዘዴዎችን በሰፊው በማስተዋወቅ፣ የአሰራር እና የህግ ማእቀፍ እንዲኖራቸው በማድረግ፣ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት ጉዳዩን የጋራ አጀንዳ እያደረገ ላለው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ያላቸውን አድናቆት የገለጹት ተሳታፊዎቹ፣ ለአተገባበሩ መሳካት ይበጃሉ ያሏቸውን የማጠናከሪያ ሀሳቦችም ሰጠዋል።
በውይይት መድረኩ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን አመራሮች ጨምሮ፣ ከክልሉ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኞች፣ ከባህርዳር እና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ከባህርዳር ዙሪያ ወረዳ ፍርድ ቤትና ከባህርዳር ከተማ ፍርድ ቤት የተወጣጡ ዳኞች እንዲሁም ጠበቆችና አቃቢ ህጎች ተገኝተዋል።
