ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

“የክልሉ ፍርድ ቤቶች በሁሉም የአፈፃፀም መለኪያዎች ሲታይ ከመቸውም ጊዜ የተሻለ የመዛግብት አፈጻጸም ማስመዝገብ ችለዋል” ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት

“የክልሉ ፍርድ ቤቶች በሁሉም የአፈፃፀም መለኪያዎች ሲታይ ከመቸውም ጊዜ የተሻለ የመዛግብት አፈጻጸም ማስመዝገብ ችለዋል” ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት

ባህርዳር ፣ ሚያዚያ 15/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት)

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አመራሮች፣ ዳኞች፣ የጉባኤ ተሿሚዎች እና ሰራተኞች የክልሉ ፍርድ ቤቶች ባለፉት 9 ወራት ያከናወኗቸውን ስራዎች ገምግመዋል።

የግምገማ መድረኩን የከፈቱት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ ፍርድ ቤቶቻችን በ2018 በጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም እንዲያስመዘግቡ በቂ ዝግጅት አድርገው እና ግልፅ እቅድ ታቅዶ ሥራ መጀመራቸውን ገልጸዋል።

የክልሉን ፍርድ ቤቶች አሰራር ቀልጣፋ፣ ተገማች፣ ፈጣን፣ ወጭ ቆጣቢ እና ተደራሽ ለማድረግ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ወራት ከ 2400 የሚበልጡ ሁሉንም የክልሉ ፍርድ ቤት ዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች በአንድ ማእከል በማግኘት ለ 10 ቀናት የቆየ ሰፊ የግንዛቤ ፈጠራ ተሰጧል ያሉት ክቡር ፕሬዝዳንቱ፣ ዳኞቹ በቆይታቸው ከሙያቸው ጋር ግንኙነት ካላቸው ስልጠናዎች በተጨማሪ፣ በአገልጋይነት፣ በመሪነት፣ በተግባቦት፣ በሙያዊ ስነ-ምግባር እንዲሁም ክልላዊ፣ ሀገራዊ እና አለምአቀፋዊ በሆኑ የምጣኔ ሀብት እና አዳዲስ የሕግና የአሰራር ማዕቀፎች ላይ ሰፊ ስልጠናዎችን ማግኘታቸውን፣ ይህም የተለያዩ ጉዳዮችን የሚያዩ፣ የተለያዩ ባለጉዳዮችን የሚያስተናግዱ ዳኞቻችን ከዳኝነት ስራቸው በተጨማሪ ነባራዊውን ሀገር እና አለምአቀፍ ሁኔታ በመረዳት በላቀ ሙያዊ ስነ-ምግባር ማህበረሰቡን እንዲያገለግሉ አስችሏቸዋል ብለዋል።

ፍትሕን ተደራሽ ለማድረግ የባሕል ፍርድ ቤቶች ላይ በቂ ጥናት አድርገን፣ 15 የባሕል ፍርድ ቤቶችን እውቅና በመስጠት ስራ ለማስጀመር በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች የባሕል ፍርድ ቤቶች የሽማግሌዎች ምርጫ ማካሄድ እና ወደ ሥራ ማስገባት ተችሏል ብለዋል።

የክልሉ ፍርድ ቤቶች፣ በ 2018 በጀት ዓመት 9 ወራት ውስጥ በመዛግብት አፈጻጸም፣ ውሳኔዎችን በአጭር ጊዜ በመስጠት፣ በመዛግብት ጥራት፣ ወጭ ፣ጊዜና ጉልበት የሚቀንሱ ዘመናዊ የዳኝነት አገልግሎት መስጫ አጋዥ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶችን በመገንባት ረገድ ከመቸውም ጊዜ የበለጠ አፈጻጸም አስመዝግበዋል ያሉት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ ተገማች የዳኝነት አገልግሎት በመስጠት ተምሳሌት የሚሆኑ ፍርድ ቤቶችን ለመገንባት የያዝነውን ርእይ ለማሳካት ሁሉም የክልሉ ፍርድ ቤቶች አመራሮች፣ ዳኞች፣ የጉባኤ ተሿሚዎችና ሰራተኞች በላቀ ተነሳሽነት ስራቸውን ማከናቸውንም ገልፀው ይህ የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል ።

የክልሉን ፍርድ ቤቶች የዲጂታላይዜሽን ትግበራ ሂደት በ 9 ወራት የስራ አፈጻጸም ግምገማው ያቀረቡት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር መኳንንት አገኘሁ( ዶ/ር)፣ፕሮጀክቱ ከተጀመረበት ከ 2017 የመጀመሪያው ወራቶች ጀምሮ እስካሁን ድረስ የተከናወኑ የዘመናዊ ዳኝነት አገልግሎት መስጫ መሰረተ ልማት ግንባታዎች ሂደት እና በቀጣይ ዙር የሚከናወኑ የፍርድ ቤቶች የዲጅታላይዜሽን ማስፋፊያ ስራዎች ላይ ያሉ እቅዶችን በዝርዝር አቅርበዋል።

በመጀመሪያው ዙር የዲጅታላይዜሽን ትግበራ ምእራፍ ፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱና በሁሉም ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ዘመናዊ የዳኝነት አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ የቴሌኮም መሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን በማከናወን አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ መቻሉን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ይህም ባለጉዳዮች ወጭ፣ ጊዜ እና ጉልበት ቆጣቢ፣ ፈጣን፣ ቀልጣፋ፣ ተደራሽና ተገማች የፍርድ ቤት አገልግሎቶችን እንዲያገኙ አስችሏል ብለዋል።

በቀጣይ፣ የመጀመሪያውን ምእራፍ የቴሌኮም መሰረተ ልማት ዝርጋታ ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ፣ ሁለተኛውን ምእራፍ የዲጅታላይዜሽን መሰረተ ልማት ዝርጋታ ማከናወን እንጀምራለን ያሉት ዶክተር መኳንንት፣ የተገልጋዩን እንግልት ፣ ወጭ እና ጊዜ የሚቀንሱ፣ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጡን ጥራት የሚጨምሩ እና የዳኞችን እና የባለሙያዎችን አቅም የሚያጎለብቱ ልዩ ልዩ የሞባይል መተግበሪያዎች እና የሶፍትዌር ስርዓቶች በተቋሙ አቅምና ከተባባሪ አካላት ጋር በመተባበር ለምተው ስራ እንደሚጀምሩ ተናግረዋል።

የክልሉን ፍርድ ቤቶች የ 9 ወራት አፈጻጸም ያቀረቡት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስትራቴጂክ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ፍሬው ታደሰ በበኩላቸው፣ በዝግጅት እና በተግባር ምእራፍ ባለፉት 9 ወራት በክልሉ ፍርድ ቤቶች የተከናወኑ ስራዎችን አቅርበዋል።

በ 9 ወራት ውስጥ በየደረጃው በሚገኙ የክልላችን ፍርድ ቤቶች 353, 695 መዛግብት ቀርበው ነበር ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ከእነዚህም ውስጥ 318, 464 መዛግብት እልባት አግኝተዋል ብለዋል።

እልባት ያገኙት መዛግብት ከተያዘው እቅድ ውስጥ 90 ከመቶ የሚሆኑት መሳካታቸውን ያሳያል ያሉት አቶ ፍሬው ታደሰ፣ ከ2017 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ብልጫ እንዳለውና፣ የተመዘገቡት አፈጻጸሞች ፍርድ ቤቶቻችን በስትራቴጂክ እቅዱ የተያዘውን እቅድ በሚያሳካ መስመር ላይ መሆናቸውን ያሳያል ብለዋል።

በቀረቡት ሪፖርቶች ላይ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ዳኞች፣ የጉባኤ ተሿሚዎች እና ሰራተኞች ያወያዩት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ ከበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ወራቶች ጀምሮ አስበን እና አቅደን ያከናወናቸው ስራዎች ውጤት አስመዝግበዋል ብለዋል።

በየደረጃው ባሉ ፍርድ ቤቶቻችን የተሻለ አፈጻጸም እንዲመዘገብ ላደረጋችሁ ዳኞቻችን እና ሰራተኞቻችን ምስጋና ይገባችኋል ያሉት ክቡር ፕሬዝዳንቱ፣ በ9 ወራት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረኩ ተገኝተው ተቋማዊ ጥያቄዎችን ላነሱላቸው የተቋሙ ሰራተኞች ምላሽና ማብራሪያ ሰጠዋል።

photo_2_2026-04-24_09-31-07
photo_3_2026-04-24_09-31-07
photo_6_2026-04-24_09-31-07
photo_5_2026-04-24_09-31-07
photo_4_2026-04-24_09-31-07
photo_7_2026-04-24_09-31-07
photo_9_2026-04-24_09-31-07
photo_8_2026-04-24_09-31-07
photo_10_2026-04-24_09-31-07
photo_13_2026-04-24_09-31-07
photo_11_2026-04-24_09-31-07
photo_12_2026-04-24_09-31-07
photo_14_2026-04-24_09-31-07

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *