ፓሪስ ፣ መጋቢት 22/2018 (የአማራ ክልል ጠ/ፍ/ቤት)
በአገራችን ኢትዮጵያ እና በክልል ደረጃ የተጀመረዉ የዳኝነት እና የፍትህ ዘርፍ መሰረታዊ የለዉጥ ሥራን ዉጤታማ ለማድረግ በተለይም አማራጭ የሙግት መፍቻ ሥርዓትን ለማጠናከር፣ የሕግ የበላይነት ለዘላቂ ሰላም ያለውን አበርክቶ ግምት ውስጥ ያስገባ አለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ማዕከል እና የሕግ የበይነት እና የሰላም ማዕከልን የሚያካትቱ ፕሮጀክቶችን ለመተግበር ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል፡፡
የተጀመሩ የለዉጥ ሥራ ፕሮጀክቶች አለም አቀፍ ደረጃ እና ጥራትን የጠበቁ ለማድረግ እንዲሁም በሂደቱ የአጋር አካላትን ድጋፍ ለማግኘት ይቻል ዘንድ የተለያዩ አገራትን ተሞክሮ በመቃኘት እና ከሚመለከታቸዉ አመራሮች ጋር ዉይይት በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለትም በክቡር ፕሬዝደንት አቶ አለምአንተ አግደው የሚመራው የልዑካን ቡድን በፈረንሳይ አገር ፓሪስ ከተማ የሚገኘው እና አለምአቀፍ የግልግል ዳኝነት (International Court of Arbitration) እና የድርድር (International Center for ADR) ማዕከላትን በስሩ በያዘዉ International Chamber of Commerce (ICC) ተቋም አደረጃጀት ላይ ምልከታ ያደረገ ሲሆን፣ ከተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ጋርም ውይይት አድርጓል፡፡
በውይይቱ ላይ ክቡር ፕሬዝደንት አቶ አለምአንተ አግደው ኢትዮጵያ የተለያዩ የሕግ እና የአሰራር ማሻሻያዎችን እያደረገች መሆኑን ጠቅሰው፣ መደበኛውን የዳኝነት ሥርዓት ለማሻሻል ከተወሰዱ እርምጃዎች በተጓዳኝ አማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴዎችን በተለይ ደግሞ የግልግል ዳኝነትን ለማጠናከር እና ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በርካታ ሥራዎች የተሰሩ መሆኑን ጠቅሰው፣ የኢንቨስትመንት እና የንግድ እንቅስቃሴ እየሰፋ የመጣ መሆኑን ተከትሎ አለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ማዕከል በኢትዮጵያ መገንባቱ ለአፍሪካዊያን የተለዬ ትርጉም ያለው መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል፡፡
International Chamber of Commerce (ICC) ያለውን ዘመናትን ያስቆጠረ ልምድ በማካፈል፣ በትብብር አብሮ በመስራት እና የሙያ ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተስፋ ያላቸው መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
በዚህ ዉይይት በፈረንሳይ የኢ.ፌ.ዲ. ሪ ልዩ መልክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር እንዲሁም በተባበሩት መንግስታት የትምህርትና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ክብርት አምባሳደር ማህሌት ሃይሉ የተሳተፉ ሲሆን፣ ጉብኝቱ አገራችን በዘርፉ ከፈረንሳይ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት እንድታጠናክር ከማገዙም ባለፈ፣ ወደፊት ተቋማቱ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር እና ልምድ ለመለዋወጥ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ይታመናል ብለዋል።
የ International Chamber of Commerce (ICC) ፕሬዝደንት የሆኑት ክላውዲያ ሳሎሞን በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ያላትን ከፍተኛ እና ስትራቴጂካል ቦታ ግምት ውስጥ በማስገባት አለም አቀፍ የግልግል ማዕከል ለማድረግ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ አበረታች መሆኑን ጠቅሰው፣ ተቋማቸው በቀጣይ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት ጋር በሁለንተናዊ መልኩ አብሮ ለመስራት እና አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
