ባህርዳር ፣ጥር 16/2018 (አብክመ ጠ/ፍ/ቤት)
የህግ የበላይነትና አማራጭ ያለመግባባት መፍቻ ዘዴዎች ለዘላቂ ሰላምና ልማት በሚል የሚካሄደው አለምአቀፍ ጉባኤ በባህርዳር ከተማ በመካሄድ ላይ ነው።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትና ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በጋራ በመሆን ባዘጋጁት በዚህ አለምአቀፍ ጉባኤ የተገኙት የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ክቡር አቶ አረጋ ከበደ በጉባኤው ለመታደም ከተለያዩ ሀገራት እና ተቋማት የመጡ ተሳታፊዎችን፣ ጉባኤውን ለመታደም እንኳን ወደ ባህርዳር መጣችሁ ብለው፣ ከተማዋ ይህንን ጉባኤ ጨምሮ ሌሎች ክልል፣ ሀገር እና አህጉር አቀፍ መድረኮችን በማዘጋጀት ላይ ትገኛለች ብለዋል።
ባህርዳር የአፍሪካ መሪዎች እና ባለድርሻ አካላት በአፍሪካ ደህንነት ጉዳዮች ላይ የሚመክሩበትን የጣና ፎረም በየአመቱ በማዘጋጀት ላይ ነች ያሉት ክቡር አቶ አረጋ ከበደ፣ ከተማዋ ለአለምአቀፍ ዳኝነት እና የግልግል ማእከል ከተማነትም እራሷን እያዘጋጀች ነው ብለዋል።
የዚህ ጉባኤ ጭብጥ የህግ የበላይነት፣ አማራጭ የለመግባባት መፍቻ ዘዴዎች እና ዘላቂ ሰላምና የልማት ጉዳዮች ከፍርድ ቤቶች ህገ መንግስታዊ ሚና እና የፍትህ አካላት ተልእኮ እንዲሁም ከክልላችን እና ከሀገራችን የመልማት ፍላጎት እና ተስፋ ጋር የተቆራኘ ነው ያሉት ክቡር አቶ አረጋ ከበደ፣ ዘላቂነት ያለው ሰላም በህግ የበላይነት ማእቀፍ የሚረጋገጥ ሲሆን፣ መደበኛ የዳኝነት እና የፍትህ ስርዓቶች ማህበረሰቡ ከሚጠቀምባቸው ያለመግባባት መፍቻ ዘዴዎች ጋር ተጣጥመው ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ ሁሉንም ወገን አሸናፊ የሚያደርግ ስራ መስራት ያስፈልገናል ብለዋል።
ለትላልቅ የሪፎርም ስራዎች አመራር እየሰጡ ላሉት የአማራ ክልል ጠ/ፍ/ቤት ፕሬዝዳንት አቶ አለምአንተ አግደው አና አመራሮቻቸው እንዲሁም ለባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በዚህ አለምአሀቀፍ ጉባኤ ተሳታፊዎች ስም ምስጋና አቀርባለሁ ያሉት ክቡር ርእሰ መስተዳደሩ፣ የክልሉ መንግስትም ይህ የፍርድ ቤቶች የሪፎርም ስራ ውጤታማ ሆኖ እንዲቀጥል በትኩረት የሕግ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ፣ የክትትልና ድጋፍ ስራ እንዲሰራ እንዲሁም ለዘርፉ በልዩ ትኩረት የበጀት ድጋፍ ጭምር በማድረግ እየሰራ ሲሆን በቀጣይም ይህንኑ ቁርጠኝነት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
