ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

“የክልላችን ሕዝብ በሺ ዘመናት ታሪኩ ካካበታቸው ዕሴቶች አንዱ የፍርድ ሥርዓት ነው”

ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ- የኢፌዴሪ ም/ጠ/ሚኒስትር

“የክልላችን ሕዝብ በሺ ዘመናት ታሪኩ ካካበታቸው ዕሴቶች አንዱ የፍርድ ሥርዓት ነው”

ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ- የኢፌዴሪ ም/ጠ/ሚኒስትር

ባህርዳር ፣ ጥር 16/2018 (አብክመ ጠ/ፍ/ቤት)

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከባህርዳር ዩኒቨርሰቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው እና ትኩረቱን በህግ የበላይነት እና አማራጭ ያለመግባባት መፍቻ ዘዴዎች ለዘላቂ ሰላምና ልማት ላይ ባደረገው አለምአቀፍ ጉባኤ ላይ የኢፌዴሪ ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር ክቡር አቶ አረጋ ከበደ እና የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደውን ጨምሮ ሌሎች የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ ሀላፊዎች፣ አምባሳደሮች፣ አለምአቀፍ የህግ ተመራማሪዎች፣የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ መንግስታዊ የሆኑ እና ያልሆኑ ድርጅቶች ሃላፊዎች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመውበታል።
በአምአቀፍ ጉባኤው የመክፈቻ ስነስርዓት ላይ ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት የኢፌዴሪ ም/ጠ/ ሚኒስትር ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የአማራ ክልል ሕዝብ ለበርካታ ዘመናት ሽምግልናን ጨምሮ የተለያዩ የዕርቅና የግልግል ዘይቤዎችን ሲጠቀም የኖረ መሆኑን ገልጸው ፣ እነዚህ ሥርዓቶች በመሠረታዊነት በመግባባት ወደ ቀደመ ጤናማ ሁኔታ በመመለስ እና ማኅበረሰባዊ ሰላምን በመፍጠር ላይ አተኩረው የተዋቀሩ ናቸው ብለዋል።
ባህላዊ አሠራሮቹ ታላላቅ አባቶችን፣ የእምነት መሪዎችን እና የሲቪክ ማኅበረሰብ መሪዎችን ይጠቀማሉ ያሉት ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የማኅበራዊ ምክክር፣ የቅሬታ ማቅረቢያ እና የቅሬታ መፍቻ መንገዶችም አሏቸው ብለዋል።
ባሕላዊ የእርቅ ስርዓቶች በተለያዩ አጋጣሚዎች ለሚከሠቱ ከንብረት ሙግት ጀምሮ ለሌሎች ከፍተኛ ጉዳት ለሚደርሱ ችግሮች ማኅበረሰባዊ ቅቡልነት ያለው መፍትሔ ያቀርባሉ ያሉት ክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ በሀገራችን እና በአማራ ክልል በተለያየ መንገድ የሚተገበሩት እነዚህ ሀገር በቀል የእርቅ ስርዓቶች በአነስተኛ ዋጋ፣ በአነስተኛ ጊዜ እና በተሻለ ቅቡልነት ፍትሕን ለማስፈን ዓይነተኛ መሣሪያ ሆነው አገልግለዋል ብለዋል።
የጎደላቸውን ሞልተን በትክክል ከተጠቀምንባቸው፣ በጉዳዮች ብዛት በከፍተኛ ጫና ውስጥ የሚገኙ መደበኛ የፍትሕ ተቋሞቻችንን ትርጉም ባለው ደረጃ ያግዛሉ ያሉት ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ አልፎም በማኅበረሰቡ ዘንድ የተሻለ ተቀባይነት እና የባለቤትነት ስሜት የሚንጸባረቅባቸውን
መፍትሔዎች ያቀርባሉ ብለዋል።
ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓቶቻችንን ከዘመናዊ ዕሳቤዎች ጋር በማስተሣሠር፣ በሕግ በመደገፍ እና አሠራሮቻቸውን በማዘመን ማዋቀር ይኖርብናል፤ በሀገራችንም ሆነ በክልላችን ተደራሽ፣ ቅቡልነት ያለው እና በመርሕ ላይ የቆመ ፍትሕን ለማስፈን እንዲቻል መደበኛና ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓቶች ተጣጥመውና ተናበው የሚጓዙበትን ዐውድ መፍጠር ይገባናል ብለዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ ከጥቂት ዓመታት በፊት ያወጣነው የግልግልና የዕርቅ ሥርዓትን የሚመራ የሕግ ማሕቀፍ፣ በቀደሙ ሕጎቻችን ላይ በተበጣጠሰ መንገድ የተቀመጡ እና ጊዜውን የማይዋጁ ድንጋጌዎችን ከማሻሻሉም በላይ፣ ዘመናዊ እና ሁሉን አቀፍ አሠራርን አስተዋውቋል ያሉት ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ በአማራ ክልል የባህል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ ሕግ መውጣት፣ ለባህላዊ ዕሴቶቻቸን ሕጋዊና ተቋማዊ ቁመና ያጎናጸፈ ርምጃ ነው ብለዋል።
በፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ማሕቀፍ የመጣው የፍርድ ቤት መር አስማሚነት አሠራር ሌላው ወሳኝ ምእራፍ ሆኖ የሚቆጠር ነው ያሉት ክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ለእነዚህ እና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉትን ጨምሮ ሊገነባቸው ያሰባቸው ማዕከላትም ሥራውን በተሻለ ዘመናዊነትና ቅልጥፍና እንድናከናው ይረዱናል ብለዋል።
በዚህ አለምአቀፍ መድረክ፣ ዓለምአቀፍ ባለሙያዎች፣ ከትምህርት ማኅበረሰቡ፣ ከፖሊሲ አውጪዎች፣ ከሲቪክ ማኅበረሰብ መሪዎች እና ከግሉ ዘርፍ ተወካዮች ጋር ጥልቅ ውይይቶች ይደረጋሉ ያሉት ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ ውይይቶቹ ተግባር ተኮር እና ችግር ፈቺ ስትራቴጂዎችን እና አሠራሮችን ለማጽናት ይረዱናል ብለዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች ከተለመደው ልማድ ወጣ ብለው፣ የማኅበረሰቡን ችግሮች በሚፈቱ እና ዕሴትን በሚጨምሩ ተጨባጭ እና ተግባራዊ ሐሳቦች ላይ እንዲያተኩሩ አደራ ያሉት ክቡር ም/ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ ይሄንን አለምአቀፍ ጉባኤ ያዘጋጁትን የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትና ባህርዳር ዩኒቨርሲቲን እናመሰግናለን ብለዋል።

photo_2026-01-26_11-32-02
photo_2026-01-26_11-32-05
photo_2026-01-26_11-32-10
photo_2026-01-26_11-32-07
photo_2026-01-26_11-32-13
photo_2026-01-26_11-32-33
photo_2026-01-26_11-32-02

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *