ባህርዳር ፣ ጥር 01/2018(አብክመ ጠ/ፍ/ቤት)
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ታህሳስ 21 እና 22/2018 ባካሄደው ልዩ መረሀ-ግብር በጥናት የለያቸውን 15 አማራጭ ያለመግባቢያ መፍቻ ዘዴዎች የክልሉ የባሕል ፍርድ ቤቶች አድርጎ እውቅና መስጠቱ ይታወቃል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የባሕል ፍርድ ቤቶችን በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ስራ ለማስጀመር እየሰራ ሲሆን፣ የዚሁ ዝግጅት አካል የሆነ የአጋር እና ባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ በተለያዩ የክልሉ ከተሞች በማካሄድ ላይ ይገኛል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፣ የአጋርና የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ በዛሬው እለት ከባህርዳር ከተማ እና ከሰሜን ጎጃም ዞን አስተዳደር ጋር አካሂዷል።
በውይይት መድረኩ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደውን ጨምሮ፣ የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው፣ የሰሜን ጎጃም ዞን አስተዳዳሪ አቶ አሰፋ ጥላሁን እና ሌሎችም አጋርና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
የውይይት መድረኩን አላማ ለተሳታፊዎች ያስረዱት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ መድረኩ የተዘጋጀው እውቅና የተሰጣቸው የባሕል ፍርድ ቤቶች በእያንዳንዱ ቀበሌ ስራቸውን እንዲጀምሩ ለማስቻል እና ይሄንን የሚያስፈጽሙ አጋርና ባለድርሻ አካላት በአዋጁ፣ አተገባበሩ እና በዝርዝር መመሪያዎች ላይ ግልጽ መረዳት እንዲኖራቸው ለማድረግ ነው ብለዋል።
የክልሉ የባሕል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፣ ለክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ፣ ለአስፈጻሚው አካል በተለይም በቀበሌ ደረጃ ላሉት አደረጃጅቶች ትልቅ ሀላፊነት ሰጧል ያሉት ክቡር ፕሬዝዳንቱ ፣ እነዚህ እና ሌሎች አዋጁን ለማስተግበር ስልጣን የተሰጣቸው ባለድርሻ አካላት ለአዋጁ ውጤታማ አተገባበር በትብብር እና በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
የአማራ ክልል የባሕል ፍርድ ቤቶች አተገባበር ፍኖተ ካርታ እና የአማራ ክልል የባሕል ፍርድ ቤቶች አፈጻጸም መመሪያ ለውይይት መነሻነት ቀርበው በተሳታፊዎቹ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ አመራሮች እና ባለሙያዎች ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ 15 የባሕል ፍርድ ቤቶችን በጥናት በመለየት እውቅና መስጠቱን አድንቀው፣ የባሕል ፍርድ ቤቶቹ በየአካባቢያቸው ተግባራዊ እንዲሆኑ ለማድረግ፣ በማስተባበር፣ ለባሕል ፍርድ ቤቶቹ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በማሟላት፣ የየአካባቢያቸውን ማህበረሰብ በማነቃነቅና የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎችን በመስራት ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።
ተሳታፊዎችን ያወያዩት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣የባሕል ፍርድ ቤቶች በአዋጁ የተሰጣቸው ስልጣን ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በንብረት ጉዳይ ምንም ገደብ ሳይደረግባቸው በሁለቱ ተከራካሪዎች ፈቃድ ላይ ተመስርተው እና በባህል እሴቱ መሰረት የመዳኘት ስልጣን ተሰጧቸዋል ያሉት ክቡር ፕሬዝዳንቱ፣ የባሕል ፍርድ ቤቶች ውሳኔ እንደመደበኛው ፍርድ ቤቶች ውሳኔ የጸና መሆኑን ጠቅሰው፣ ከሁለቱ ወገኖች አንዱ ለውሳኔው ተገዥ ባይሆን የወረዳ ፍርድ ቤቶች ውሳኔውን የማስፈጸም ግዴታ እንዳለባቸው አስታውቀዋል።
የባሕል ፍርድ ቤቶች ቀላል የሆኑ ማህበረሰቡ የሚያውቃቸውን ስነ-ስርዓቶችን የሚከተሉ፣ በአቅራቢያቸው የሚገኙ ተደራሽ እና ወጪ ቆጣቢ ናቸው ያሉት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ እነዚህን አማራጭ ያለመግባቢያ መፍቻ የባሕል ፍርድ ቤቶች በየአካባቢዎች ተግባራዊ በማድረግ ህብረተሰቡ ፍትሕን በደጅ እንዲያገኝ ሁሉም አጋርና ባለድርሻ አካላት የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት ብለዋል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዛሬ ከባህርዳር ከተማ እና ከሰሜን ጎጃም አስተዳደር ጋር ያካሄደው የአጋርና የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ በሌሎች የክልሉ አካባቢዎችም የሚቀጥል ይሆናል።






