ASC Logo

Amhara Region

Supreme court

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለዳኞች፣ሬጅስትራሮች፣ችሎት ፀሐፊዎችና የስካኒግ ባለሙያዎች በኢ-ፋይሊንግ ሲስተም(Electronic Filing System) አጠቃቀም ላይ ስልጠና ሰጠ

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለዳኞች፣ሬጅስትራሮች፣ችሎት ፀሐፊዎችና የስካኒግ ባለሙያዎች በኢ-ፋይሊንግ ሲስተም(Electronic Filing System) አጠቃቀም ላይ ስልጠና ሰጠ

ባህርዳር፣ ታህሳስ 12/2018 (አብክመ ጠ/ፍ/ቤት)

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የክልሉን ፍርድ ቤቶች የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ፣ ወጪ እና ጊዜ ቆጣቢ በማድረግ ላይ ይገኛል።

በሁሉ-አቀፍ የለውጥ ስራ ላይ የሚገኘው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፣ እየተገበራቸው ካሉ የለዉጥ ስራዎች መካከል የኢ- ፋይሊንግ ሲስተም (Electronic Filing System) አንዱ ሲሆን ይህ ሲስተም የተለያዩ ሶፍትዌሮች  (software platforms) አማካኝነት የሚሰራ ሲሆን የፍ/ቤት ተገልጋዮች አቤቱታ ለማቅረብ እና መዝገብ ለማስከፈት ጉዳዩ ወደሚታይበት ፍ/ቤት በአካል መምጣት ሳያስፈልጋቸዉ ባሉበት አካባቢ ሆነዉ መዝገብ የሚያስከፍቱበት እና  አቤቱታ የሚያቀርቡበት ሲሆን፣ ካሁን በፊት በእጅ ከቦታ ቦታ እና ከክፍል ክፍል ይንቀሳቀሱ የነበሩ መዛግብትን ከእጅ ንክኪ ነጻ በሆነ መንገድ በሲስተም  እንዲልኩ ፣ ባለጉዳዮች፣ የሪጅስትራር ሰራተኞች ፣የችሎት ጸሐፊዎች እና  ዳኞች መዛብቱን በሲስተም እንዲላላኩ የሚያስችል አሰራር ነው።

በቴክኖሎጂው አሰራር ላይ በሂደቱ ውስጥ የሚያልፉ ዳኞች ፣ የሪጅስትራር  እና የስካነር ባለሙያዎች እንዲሁም የችሎት ጸሐፊዎች በተዘረጋው የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ላይ እንደዬ ኃላፊነታቸው እና የሥራ ድርሻቸው መዝገቡን በምን አግባብ እንደሚላላኩ፣ መዝገቡ እንዴት እንደሚመዘገብ እና በአጠቃላይ ቴክኖሎጂውን እንዴት ውጤታማ በሆነ መልኩ ጥቅም ላይ ማዋል እንዳለባቸው ታህሳስ 11 ቀን 2018 ዓ.ም በጠቅላይ ፍ/ቤት አዳራሽ ስልጠናውን ወስደዋል።

ስልጠናውን የሰጡት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር መኳንንት አገኘሁ (ዶ.ር) ሲሆኑ፣ ዳኞች፣ የስካነር እና የሪጅስትራር ባለሙያዎች እንዲሁም የችሎት ጸሐፊዎች የለማውን የኢ- ፋይሊንግ ዘመናዊ የመዝገብ መክፈቻ እና መላላኪያ ስርዓት በምን አግባብ እና እንዴት መጠቀም እንደሚችሉ ተግባር ተኮር ስልጠና ሰጠዋል።

ተግባር ተኮር ስልጠናውን የወሰዱ ዳኞች፣ የሪጅስትራር እና የስካነር ባለሙያዎች እንዲሁም የችሎት ጸሐፊዎች ለእያንዳንዳቸው በተዘጋጀ መለያ ስም እየገቡ እና  ለናሙና የተዘጋጁ መዝገቦችን እንዴት እና በምን አግባብ መክፈት እና መላላክ እንዳለባቸው ያዩ ሲሆን፣ ግልጽ ያልሆኑላቸውን አሰራሮች እያነሱ በአሰልጣኙ እና በሌሎች የዳይሬክቶሬቱ ባለሙያዎች ምላሽ ተሰጦባቸዋል።

በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ እየተገበራቸው ያሉ  ዘመናዊ የዳኝነት አገልግሎት መስጫ አማራጮች ተቀዳሚ አላማ የተገልጋዩን  እንግልት ወጭ እና ጊዜ መቀነስ እንዲሁም ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለዉ አሰራር እዉን ማድረግ ነው ብለዋል።

ፕሬዘዳንቱ ፤ የጀመርነው የኢ- ፋይሊንግ አገልግሎት ባለጉዳዮች ባህር-ዳር ወደሚገኘዉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ወይም የጠቅላይ ፍ/ቤት ምድብ ችሎት ወደሚገኝባቸዉ ደብረ-ማርቆስ፣ደብረ-ብርሃን፣ደሴ እና ጎንደር በአካል መሄድ ሳያስፈልጋቸዉ፣  ባሉበት አካባቢ ወዳሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች በመሄድ መዝገባቸውን በዲጅታል መንገድ በማስክፈት ጉዳዩ ወደሚታይበት ጠቅላይ ፍ/ቤት የኢ-ፋይልንግ ሲስተሙን በመጠቀም የሚላኩበት እና ለአላስፈላጊ እንግልቶች እንዳይዳረጉ የሚከላከል ነዉ ብለዉ፣ ይህንን አገልግሎት በ2019 ዓ.ም የበለጠ በማስፋት እና እስከ ወረዳ በማድረስ ተገልጋዮች በሚቀርባቸዉ ወረዳ በመገኘት የከፍተኛ እና የጠቅላይ ፍ/ቤት ፋይሎችን የሚከፍቱበትን ዘመናዊ አሰራር እንተገብራለን ብለዋል።

ኢ- ፋይሊንግ ፤ በዳኞች ፣ ችሎት ጸሐፊዎች፣ ሪጅስትራር እና ስካነር ባለሙያዎች መካከል በሀርድ ኮፒ መዝገቦችን ከማመላለስ ይልቅ ዲጅታል ቴክሎጅን በመጠቀም በመላላክ ወጭን፣ ጊዜን እና ጉልበትን በመቀነስ እንዲሁም መዝገቦችን ከሰው ንክኪ ነጻ በማድረግ ግልጸኝነትን እና ተጠያቂነትን በማስፈን ታማኝነትን ያረጋገጠ የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት ያስችለናል ያሉት ክቡር ፕሬዝዳንቱ፣  ለዚህ እና ለሌሎች የጀመርናቸው አዳዲስ የአገልግሎት መስጫ አማራጮች ተግባራዊነት በየደረጃው ባሉ ፍርድ ቤቶቻችን የሚሰሩ አመራሮች ፣ ዳኞች እና ባለሙያዎች በትጋትና በቅንነት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

ዳኞች እና አጠቃላይ የፍ/ቤቱ ባልደረቦች የዲጅታላይዜሽን ትግበራን የሥራቸዉ አንድ አካል አድረገዉ መዉሰድና በትብብር መስራት ያለባቸዉ መሆኑን ገልጸዉ፣  በተለይም አመራሮች አንዱ የሚለኩበት ኃላፊነታቸዉ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ፍ/ቤቱ ከኢ-ፋይሊንግ በተጨማሪ በቴክኖሎጅ የተደገፈ የርቀት ክርክርን (Remote litigation using or through smart courts) ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን እና በተለይም በጎንደር ፣ደሴ ፣ደብረ ማርቆስ እና ደብረ ብርሃን እስከአሁን ከተገነቡት አንድ አንድ ስማርት ችሎቶች በተጨማሪ በእያንዳንዳቸዉ ተጨማሪ ሁለት ሁለት ስማርት ችሎቶችን በማጠናቀቅ ሂደት ላይ መሆኑን ጠቅሰዉ፣ አንዳንድ የፍ/ቤቱ ባልደረቦች (ዳኞችና ሌሎች ሠራተኞች) የተጀመረዉ የቴክኖሎጅ ትግበራ ከሥራ ቦታችን ሊያፈናቅለን ይችላል በሚል ፤ በተመሳሳይ አንዳንድ ጠበቆች ደግሞ የጉዳዮች ፍሰት ስለሚቀንስ ገበያ ይቀንስብናል እንዲሁም ጉዳያችን በምናዉቃቸዉ ዳኞች ሊታይ ይገባል በሚል መነሻ በምድብ ችሎቶች ይሰጥ የነበረዉ  የዳኝነት አገልግሎት ቀሪ እንደተደረገ አስመስለዉ በሶሻል ሚዲያ ጭምር ቅስቀሳ ማድረጋቸዉ ተገቢነት የሌለዉ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ፍ/ቤቱ ተገልጋዮችን ጨምሮ ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር ተከታታይ ዉይይቶችን የሚያደርግ እና ለፈፃሚዎች የሚሰጠዉን ስልጠና ደግሞ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡ በየደረጃዉ ላሉ የአማራ ክልል ፍ/ቤት ባልደረቦች ሲሰጥ የቆየዉ ስልጠና በቀጣይ ለዐቃቢያነ-ሕግ፣ ጠበቆች እና ነገረ-ፈጆች እንዲሁም ለማረሚያ ቤት ኦፊሰሮች እና አመራሮች  የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

አሁን በተጀመረዉ የዲጅታላይዜሽን ሥራ ከዚህ በፊቱ ከነበረዉ በተሻለ መልኩ አገልግሎቱን ለህብተሰቡ ቅርብ የማድረግ ዓላማ ያለዉ ሲሆን፣ ከምድብ ችሎት ወደ ባህር ዳር የሚመጣ ተገልጋይ እንደማይኖር እንዲያዉም ከሰቆጣ ፣ከወልዲያ እና ከከሚሴ አካባቢ ወደ የጠቅላይ ፍ/ቤት ደሴ ምድብ ችሎቶች በአካል ይመጡ የነበሩ ተገልጋዮች ደሴ መምጣት ሳያስፈልጋቸዉ አቅራቢያቸዉ ወደ ሚገኘዉ ከፍተኛ ፍ/ቤት በመሄድ ኢ-ፋይሊንግ እና የርቀት ክርክርን በመጠቀም የጠቅላይ ፍ/ቤትን መዝገቦች እና አቤቱታ ማስከፈትን ጨምሮ ባሉበት ሆነዉ ክርክር ማድረግ የሚችሉበት ሁኔታ እየተፈጠሩ መሆኑን ይህም የዜጎቻችንን እንግልት ፣ወጭ እና  ጊዜ በእጅጉ የሚቀንስ ነዉ ብለዉ፣ ከተጀመረዉ የለዉጥ ሥራ ሥፋት አንጻር ፍ/ቤቱ ተጨማሪ የሰዉ ሃይል ይፈልግ ካልሆነ በስተቀር የሠራተኛ መፈናቀል እንደማይኖር ፕሬዘዳንቱ በገለጻቸዉ አረጋግጠዋል፡፡

ዜጎችም ሆነ ጠበቆች ነጻ (ትክክለኛ) ዳኝነት የማግኘት እንጅ ጉዳያቸዉን የሚያዉን ዳኛ የመምረጥ መብት እንደሌላቸዉ ፤ ዳኞች የሚመለመሉት እና የሚሾሙት በሙያ ችሎታቸዉ እና ለሁሉም ግልጽ በሆነ መስፈርት እና ሁሉም በተጋበዘበት ግልጽ ዉድድር መሆኑን ፤ የዳኝነት ወይም የፍትህ አገልግሎት አለምአቀፋዊ ይዘት ያለዉና በድንበር እና በአካባቢ የማይከለል መሆኑን፣ ዳኞችን መድቦና አዘዋዉሮ የማሰራት ተግባር ደግሞ የፍ/ቤቱ ኃላፊነት ብቻ መሆኑን ተገንዘቦ እና የፍ/ቤት አስተዳደር እና የዳኝነት ነጻነትን አክብሮ መስራት እንደሚገባ አያይዘዉ ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም የጠቅላይ ፍ/ቤት ጎንደር ፣ደሴ ፣ደብረ ማርቆስ እና ደብረ-ብርሃን ምድብ ችሎት ተገልጋዮች አገልግሎት ለማግኘት (ፋይል ለማስከፈትም ሆነ ለክርክር ) ወደ ባህር-ዳር በአካል መምጣት ሳያስፈልጋቸዉ እንደከዚህ በፊቱ ሁሉ ወደ የምድብ ችሎት እና በአማራጭ በአቅራቢያቸዉ ወደሚገኙ ከፍተኛ ፍ/ቤቶች በመሄድ አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉ ገልፀዉ፣ የሕዝብ እንግልት ለመቀነስ ተብለዉ የሚተገበሩ የዚህ አይነት የለዉጥ ሥራዎችን መደገፍ እና የፍትህ ስርዓቱ አጋዥ መሆን ፤ ግልጽ ባልሆኑ ጉዳዮች መረጃ መጠየቅ ሲገባ አንዳንድ የፍ/ቤቱ ባልደረቦች፣ ጠበቆች  እና የሌሎች የፍትህ ተቋማት ባልደረቦች የተናበበ በሚመስል ምልኩ ጉዳዩን ካልተገባ የግል ጥቅም አንጻር ብቻ በማየት የፍ/ቤቱን የአሰራር ነጻነት በሚነካ ተግባር ዉስጥ ከመግባት እና የተዛባ መረጃ ከማስተላለፍ ተቆጥበዉ የሙያ ሥነ-ምግባራቸዉን አክብረዉ እንዲሰሩ ፍ/ቤቱ በድጋሜ ጥሪዉን ያቀርባል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *