ባሕርዳር ፣ ነሐሴ 28/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እየተገበራቸው ካሉ የተቋምና የሰው ሀይል አቅም ግንባታ፣ የዘመናዊ ዳኝነት አገልግሎት መስጫ መሰረተ ልማቶች ዝርጋታ በተጨማሪ፣ የሀገሪቱን እና የክልሉን የዳኝነት እና የፍትሕ ስርዓት ከጥንታዊ አሰራር እስከ ዘመናዊው ስርዓት የሚዳስስ የፍትሕ ሙዚየም ግንባታ ይገኝበታል።
ለሙዚየሙ የሚሆን ዘመናዊ ሕንጻ ከመገንባት እስከ መዚየሙ ማደራጀት እና ለጎብኝዎች ክፍት ማድረግ በርካታ ሂደቶችን ያለፈው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፣ በዛሬው እለት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ክቡር አቶ አረጋ ከበደን ጨምሮ፣ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የተከበሩ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ፣ የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት መንገሻ አየን (ዶ/ር)፣ የአማራ ክልል ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጀነራል ጥጋቡ ይልማ፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደሕንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ጉታ እና ሌሎችም እንግዶች በተገኙበት በይፋ ተመርቆ ለጎብኝዎች ክፍት ሆኗል።
በመረሀግብሩ ላይ የሙዚየሙን መገንባት እና መደራጀት አስፈላጊነት ለእንግዶቹ ያስረዱት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ የዳኝነት እና የፍትሕ ሥርዓቱ የሀገሪቱ ታሪክ አንድ አካል መሆኑን ገልጸው ፣ ይህንን ታሪክ አደራጅቶ ለትውልድ ለማስተላለፍ፣ ትውልዱ የሀገሪቱን የዳኝነት እና የፍትሕ ሥርዓት ከጅማሮው ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ መረዳት እንዲኖረው ታስቦ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሙዚየሙን ለማደራጀት ዘመናዊ ሕንጻ ከመገንባት ጀምሮ፣ ለሙዚየሙ ግብዓት የሚሆኑ ታሪካዊ ሰነዶችን፣ መዛግብትን፣ የፎቶ፣ የድምጽ እና የቁሳቁስ ግብዓት ለመሰብሰብ እና ለማደራጀት ከክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ጨምሮ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሌሎቾ የሥራ ክፍል ሀላፊዎችን ያካተተ ቡድን ተቋቁሞ ዓመቱን ሙሉ ሲሠራ መቆየቱን አስታውቀዋል።
የሙዚየሙ በሀገሪቱ የዳኝነት እና የፍትሕ ሥርዓት ላይ ምርምሮችን ለሚያካሂዱ ተመራማሪዎች፣ የሕግ ተማሪዎች፣ ዩኒቨርስቲዎችና ሌሎች ተቋማትና ግለሰቦች በማጣቀሻነት የሚያገለግሉ የሰነድና የምስል ክምችቶች አሉት ያሉት ክቡር ፕሬዝደንቱ፣ ለፖሊሲ እና ሌሎች የዳኝነት እና የፍትሕ ስትራቴጂክ ሰነዶች ዝግጅት የሚያገለግሉ ግብዓቶች የሚገኙበት ማእከልም ነው ብለዋል።
የፍትሕ ሙዚየሙ በከፊል ዲጂታል ሆኖ የተደራጀ ሲሆን፣ የሕግ ተማሪዎች እና እጩ ዳኞች የሚለማመዱበት ምስለ ችሎት ጨምሮ መደበኛ ችሎት መከታተል የሚችሉበትን የዲጂታል አገልግሎት የያዘ ነው።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፍትሕ ሙዚየም ከዛሬ ጀምሮ ለጎብኚዎች ክፍት ተደርጓል።








