ባሕርዳር፣ ነሐሴ 23/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የክልሉን ፍርድ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ በመሰረታዊነት ማሻሻል የሚችሉ በርካታ የለውጥ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል።
በዘመናዊ የዳኝነት አገልግሎት መስጫ መሰረተ ልማቶች ዝርጋታ፣ በተቋም እና በሰው ሃይል አቅም ግንባታ የተገልጋዮችን ወጭ፣ እንግልት፣ ጊዜ እና ጉልበት በመቀነስ፣ ቀልጣፋ፣ ተገማች እና አመኔታን ያተረፈ የዳኝነት አገልግሎት በየደረጃው ባሉ የክልሉ ፍርድ ቤቶች ለመስጠት እየሠራ የሚገኘው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አርአያነት ያላቸውን የለውጥ ሥራዎች አከናውኗል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጀነራል ጥጋቡ ይልማ፣ የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጀነራል አስራት ዴኔሮ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር እርዚቅ ኢሳ እና ሌሎች የፖሊስ አባላት በዛሬው እለት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ስር ነቀል የለውጥና የማሻሻያ ስራዎች ጎብኝተዋል።
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን የዲጅታላይዜሽን መሰረተ ልማቶች፣ ዘመናዊ የሕጻናት ማቆያ፣ ግልጽ እና የርቀት ክርክር የሚካሄድባቸው ዘመናዊ የችሎት አዳራሾች፣ የአንድ ማዕከል ዲጅታል አገልግሎት እና ባለጉዳዮች የፈለጉትን መረጃ ማግኘት የሚችሉበትን የጥሪ ማዕከል ጨምሮ በዘመናዊ መልኩ የተደራጀውን የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፍትሕ ሙዚየም ጎብኝተዋል።
እንግዶችን ተቀብለው፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የተገበራቸውና እየተገበራቸው ያሉ የዘመናዊ የዳኝነት መስጫ መሠረተ ልማቶች፣ በተቋም ግንባታ እና በምቹ የሥራ ከባቢ ፈጠራ የተሠሩ ሥራዎችን ያስረዱት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፍትሕ ሙዚየም እንደ ሀገር እና በክልል ደረጃ የዳኝነት እና የፍትሕ ስርዓቱ
ከጥንት ጀምሮ የመጣበትን ሂደት፣ ዘመናዊ የዳኝነት እና የፍትሕ ስርዓት በጊዜ እና በድርጊት ቅደም ተከተል ለፍትሕ ስርዓቱ ባለድርሻ አካላት እና ለትውልዱ ለማሳየት መደራጀቱን ተናግረዋል።
የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጀነራል አስራት ዴኔሮ እና የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጀነራል ጥጋቡ ይልማ፣በበኩላቸው፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ተገኝተው ባዩት ነገር፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የክልሉን ፍርድ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል በዘረጋቸው መሰረተ ልማቶች መደነቃቸውን ገልጸዋል።
በተቋም ግንባታ ትልቁ ችግር የተጀመሩ የለውጥና የማሻሻያ ስራዎችን ታች ማድረስ ነበር ያሉት አዛዦቹ፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ዘመናዊ የዳኝነት አገልግሎት መስጫ መሰረተ ልማቶችን መዘርጋት በጀመረ በአጭር ጊዜ ውስጥ፣ ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አልፎ በሁሉም ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች እና በ 27 ወረዳ ፍርድ ቤቶች ተግባራዊ ማድረጉ በትክክለኛ የተቋም ግንባታ ሂደት ላይ ለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የተገበራቸው ወረቀት አልባ የዳኝነት አገልግሎቶች እና ሌሎች የለውጥና የማሻሻያ ስራዎች በተሞክሮነት የሚወሰዱ ናቸው ያሉት አዛዦቹ፣ በጋራ በሚያገኗኛቸው ጉዳዮች ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጋር በትብብር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።












