ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

አማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአስተዳደር ሠራተኞች የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ እና የ 2019 በጀት ዓመት እቅድ ውይይት አካሄዱ

አማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአስተዳደር ሠራተኞች የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ እና የ 2019 በጀት ዓመት እቅድ ውይይት አካሄዱ

ባሕር ዳር ፣ ነሐሴ 18/2018 (የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት)

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የክልሉን ፍርድ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ በመሰረታዊነት በማሻሻል ህብረተሰቡ ፈጣን፣ ተገማች፣ ወጭ እና ጊዜ ቆጣቢ አገልግሎት እንዲያገኝ ለማስቻል በበርካታ የለውጥ ሂደቶች ውስጥ እያለፈ ይገኛል።

የተጀመሩ ሁሉአቀፍ የለውጥና የማሻሻያ ስራዎች ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንዲችሉ እና ዘላቂነት እንዲኖራቸው በየደረጃው የሚገኙ ፍርድ ቤቶች አመራሮች፣ ዳኞች፣ የጉባኤ ተሿሚዎች እና ሰራተኞች የድርሻቸውን በመወጣት ላይ ሲሆኑ፣ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎችን በመተግበር እና በማስቀጠል ላይ የሚገኙት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሠራተኞች የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም በመገምገም፣ በቀጣይ በጀት ዓመት እቅድ ላይ ውይይት አድርገዋል።

በግምገማ እና እቅድ ውይይቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ሙሉዓለም ቢያዝን፣ በበጀት ዓመቱ የክልሉ ፍርድ ቤቶች የተሻለ አፈጻጸም ያስመዘገቡ መሆኑን ጠቅሰው፣ ምንም እንኳን የፍርድ ቤቱ አመራሮች በበላይነት ቢመሩትም፣ ለዚሕ ለውጥ እና ውጤት ያበቃን በየደረጃው የሚገኙ ዳኞችና ሰራተኞች የጋራ እና ተናባቢ ስራ በመሆኑ ይሄንን በቀጣዩ በጀት ዓመት ስራችንም የበለጠ አጠናክረን ማስቀጠል ይኖርብናል ብለዋል።

የክልሉን ፍርድ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ በመሰረታዊነት ለማሻሻል ከአጋርና ባለድርሻ አካላት ግር ሰፊ የትብብር ስራ ተሰርቷል።

ከተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች አገልግሎታችንን ፈልጎ የሚመጣን ባለጉዳይ ወጭ እና ጊዜ ቆጣቢ የሆነ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ከሁላችንም ይጠበቃል ያሉት ምክትል ፕሬዝደንቱ፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ተግባራዊ ባደረግናቸው የዘመናዊ ዳኝነት አገልግሎት መስጫ መሰረተ ልማቶች ምቹ ባለሆነ ሁኔታ ወደ ማእከል የሚመጡ ባለጉዳዮችን እንግልት ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ችሏል ብለዋል።

አሁን ላይ ምስክሮች ከውጭ ሀገራት ጭምር ባሉበት ሆነው የምስክርነት ቃላቸውን እየሰጡ ነው ያሉት አቶ ሙሉዓለም ቢያዝን፣ የዳኝነት ስራ በአንድ ተቋም ብቻ የሚከናወን ባለመሆኑ ከሌሎች የፍትሕ ተቋማት ጋር በትብብር እና በቅንጅት መስራታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

በዲጅታል የዳኝነት አገልግሎት መስጫ አማራጮች እና የባሕል ፍርድ ቤቶችን ጨምሮ በሌሎች አማራጭ ያለመግባባት መፍቻ ዘዴዎች ጥራቱን የጠበቀ እና ተደራሽ የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት በስፋት ይሰራል ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሙሉዓለም ቢያዝን፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የጀመራቸው የለውጥና የማሻሻያ ስራዎች ሙሉ በሙሉ መተግበር እንዲችሉ በየደረጃው ያሉ የፍርድ ቤታችን ሰራተኞች በጀመሩት ጥረት ስራቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።

በግምገማ እና እቅድ ትውውቅ መድረኩ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ምድብ ችሎቶችን ጨምሮ ሁሉም ሠራተኞች የተገኙ ሲሆን፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስትራቴጂክ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ፍሬው ታደሰ፣ ከ2016 እስከ 2018 የተተገበረውን የክልሉ ፍርድ ቤቶች የትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈጻጸምና የ2019 በጀት ዓመት እቅድ አቅርበዋል።

የክልሉ ፍርድ ቤቶች የተደራሽነት፣ ቅልጥፍና እና ጥራት ችግሮች፣ አገልግሎት አሰጣጡ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አለመሆን፣ የሰው ሃብት ልማት ስራዎች በሚፈለገው ልክ ትኩረት ሳይሰጣቸው መቆየቱ፣ ከአጋር አካላት ጋር የነበረው ግንኙነት የፍርድ ቤቶችን ነጻነት የሚገፋ የነበረ መሆኑን እንዲሁም ከስነ-ምግባር ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮች በቀደሙት አመታት ይስተዋሉ እንደነበር በሪፖርታቸው የጠቀሱት አቶ ፍሬው፣ በሶስት ዓመቱ የትራንስፎርሜሽን ትግበራ ችግሮችን ለመቅረፍ በሰፊው መሰራቱንና በዚህም አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

ለትራንስፎርሜሽኑ ትግበራ እቅድ መነሻ የሆኑ ምክንያቶችን፣ የተተገበሩ የለውጥና የማሻሻያ ስራዎችን እና ያስገኙትን ውጤት በሪፖርታቸው ያመላከቱት አቶ ፍሬው፣ ከክልሉ መንግስት የ25 ዓመት አሻጋሪና ዘላቂ የእድገትና የልማት እቅድ፣ የፍርድ ቤቶች የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድና ከ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም እንዲሁም ከ2016 እስከ 2018 በጀት ዓመት ሲተገበር የቆየውን የዳኝነት ትራንስፎርሜሽን እቅድ መነሻ በማድረግ የ2019 በጀት ዓመት እቅድ መዘጋጀቱን አብራርተዋል።

በቀረቡት የእቅድ አፈጻጸም እና የቀጣይ በጀት ዓመት እቅድ መነሻነት ሀሳብና አስተያይታቸውን የሰጡ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሰራተኞችም፣ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የጀመራቸው የለውጥና የማሻሻያ ስራዎች የተገልጋዮችን ወጭ እና እንግልት በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣታቸውን በቅረበት መታዘብ እንደቻሉ ጠቅሰው፣ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ጥያቄዎችን አቅርበው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጦባቸዋል።

ከሰራተኞቹ ለተነሱ ጥያቄዎች የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ እንዳደለው አይተንፍሱ ፣ የፕሬዝደንቱ ልዩ አማካሪ ወርቁ ያዜ(ረ/ፕ) እንዲሁም የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ስትራቴጂክ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ፍሬው ታደሰ ዘርፋቸውን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ ሰራተኞችን ያወያዩት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ሙሉአለም ቢያዝን ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጠዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *