



በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት የተመራ የክልሉ የፍትህ እና ህግ ኢንስትቲዩት የበላይ አመራር እና የቦርድ አባላት በፌደራል ፍትህ እና ህግ ኢንስትቲዩት እንዲሁም በኦሮሚያ የፍትህ ባለሙያዎች ማሰልጠኛ ማዕከል ጉብኝት አደረጉ
አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 04/2017 ዓ.ም(አብክመ ጠ/ፍ/ቤት)
በአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር ፣ 4ኛ ዓመት ፣ 9ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የፍትህ እና ህግ ኢንስቲትዩት እንደገና ማቋቋሚያ አዋጅ የፀደቀ ሲሆን ፣ ህጉም ኢንስቲትዩቱን ገለልተኛ እና ጠንካራ የሆነ የልህቀት ማዕከል እንዲሆን ለማስቻል የሚረዳ ሲሆን ፣ የኢንስቲዩቱ ተጠሪነት ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ እንዲሆን እና የተለያዩ የአደረጃጀት እና የአሰራር ስርዓቶችን ዘርግቷል፡፡
ኢንስቲትዩትም እንደ አዲስ በተቋቋመበት አግባብ የቦርዱ ሠብሳቢ እና የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዘዳንት የሆኑት አቶ አለምአንተ አግደው ፣ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ደሴ ጥላሁን (ዶ/ር) ፣ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ አበራ እና በአዲስ የተዋቀረው የሥራ አመራር ቦርድ አባላት በፌደራል የፍትህ እና ህግ ኢንስትቲዩት እና የኦሮሚያ የፍትህ ባለሙያዎች ማሰልጠኛን ጎብኝተዋል፤
የተደረገው ጉብኝት እና ውይይቱ ከሁለቱም ተቋማት የበላይ አመራሮች ጋር ስለየተቋማቱ የአሰራር ሰርዓት ፣ መልካም ተሞክሮዎች፣ የሚያጋጥሙ ችግሮች እንዲሁም በጋራ የሚሰሩባቸው ጉዳዩች ብሎም እንደ አገር ተናባቢ እና ጠንካራ ተቋማትን መገንባት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የመከሩ ሲሆን ፣ ይህም የአማራ ክልል የፍትህና ህግ ኢንስቲትዩት የያዛቸውን ዘርፈ ብዙ ሃላፊነቶች እና የለውጥ ጉዞ በተሻለ ተግባራዊ ለማድረግ መልካም ልምድ የሚሆን እና ለወደፊት በጋራ ለሚሰሩ ሥራዎችም መሰረት የጣለ ነው፡፡
