ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

የአማራ ክልል የፍትሕና የህግ ኢኒስቲትዩት የ17ኛ ዙር የቅድመ ስራ ሰልጣኞችን  አስመረቀ

የአማራ ክልል የፍትሕና የህግ ኢኒስቲትዩት የ17ኛ ዙር የቅድመ ስራ ሰልጣኞችን  አስመረቀ

ባህርዳር፣ ህዳር 15/2018 (አብክመ ጠ/ፍ/ቤት)

የአማራ ክልል የፍትሕና የህግ ኢኒስቲትዩት ላለፉት 20 ዓመታት በርካታ ቁጥር ያላቸውን ዳኞችና አቃቢያነ ህጎች በማሰልጠን ፣ ለክልሉ እና ለሀገሪቱ የዳኝነት እና የፍትሕ ስርዓት መሻሻል ጉልህ አስተዋጽኦ ሲያደርግ ቆይቷል።

ኢኒስቲትዩቱን ጠንካራ የስልጠና ፣ የምርምር እና የፍትሕ መረጃ ማዕከል ለማድረግ የለውጥ እና ተቋማዊ የማሻሻያ ስራዎች እየተደረጉ ሲሆን ፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ2017 በጀት ዓመት ካከናወናቸው ስራዎች አንዱ  ኢኒስቲትዩቱን እንደገና በማደራጀት እና ተጠሪነቱን ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በማድረግ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን የተጀመረው እንቅስቃሴ ተጠቃሽ ነው።

ኢኒስቲትዩቱ ፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ስር እንደገና በተደራጀ ማግስት ለመጀመሪያ ጊዜ ለ8 ወራት በንድፈ ሀሳብ እና በተግባር ያሰለጠናቸውን የ 17ኛ ዙር የቅድመ ስራ ሰልጣኞች አስመርቋል።

የምረቃ መረሀግብሩን የከፈቱት የኢኒስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ደሴ ጥላሁን (ዶ/ር) ተመራቂዎቹን ፣ በበርካታ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ አልፋችሁ እዚህ በመድረሳችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና አመራሮች፣ የክልሉ መንግስት እንደ ክልል የዳኝነት እና የፍትሕ ስርዓቱን ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት ውስጥ የወሰዱትን ቁርጠኛ አቋም ያደነቁት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ወደ ዳኝነት እና አቃቢያነ ህግነት ሙያ ለሚቀላቀሉ የቅድመ ስራ ሰልጣኞች የተሰጠው ተግባር ተኮር ስልጠና፣ እጩ ዳኞች እና አቃቢያነ ህጎቹ በእውቀት ፣ በክህሎት እና በላቀ ሙያዊ ስነምግባር ማህበረሰባቸውን በቅንነት እና በታማኝነት እንዲያገለግሉ በቂ አቅም የፈጠረ ነው ብለዋል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ እጩ ዳኞች እና አቃቢያነ ህጎች ማህበረሰባቸውን በፍጹም ሙያዊ ስነ-ምግባር ፣ በላቀ የአገልጋይነት መንፈስ እና ቁርጠኝነት ለማገልገል ያላቸውን ዝግጅት በተመለከተ በተወካያቸው አማካኝነት መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፣ ከዳኝነት እና ከፍትሕ ስርዓቱ ጋር የተያያዙ ፣ ከሙያዊ ስነ-ምግባር እና ህዝብን በታማኝነት ማገልገል የዳኝነት እና የፍትሕ ባለሙያዎቹ ተቀዳሚ ሀላፊነት መሆኑን የሚያስገነዝቡ የስነ-ጽሁፍ ስራዎች ቀርበዋል።

የቅድመ ስራ ሰልጣኞችን መመረቅ ያበሰሩት እና ለተመራቂዎቹ የስራ መመሪያ ያስተላለፉት ፣ የእለቱ የክብር እንግዳ፣ የኢኒስቲትዩቱ የቦርድ ሰብሳቢ እና የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው፣ በክልሉ የዳኝነት እና የፍትሕ ማሻሻያ ላይ እየተደረጉ ያሉ የለውጥ ስራ ማሻሻያዎች ቀጣይነት ያለው ተቋማዊ ግንባታን ታሳቢ አድርገው መከናወናቸውን ተናግረዋል።

የክልሉን የዳኝነት እና የፍትሕ ስርዓት አገልግሎት አሰጣጥ በዘላቀነት ለማሻሻል ኢኒስቲትዩቱ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ስር ሆኖ እንደገና እንዲደራጅና በርካታ የአሰራር ማሻሻያዎች ተቋሙ ላይ በተካሄዱበት ማግስት ፣ እንዲሁም የክልሉ መንግስት የዳበረ የዳኝነት እና የፍትሕ ስርዓት ለዘላቂ ልማት እና ጤናማ የህብረተሰብ መስተጋብር ያለውን ድርሻ በመረዳት እየወሰድናቸው ያሉ የማሻሻያ ስራዎችን በላቀ ቁርጠኝነት እያገዘ ባለበት ሰዓት መመረቃቸውን የገለጹት ክቡር ፕሬዝዳንቱ፣ ተመራቂዎች ሙያችሁን እና የተሰጣችሁን ሀላፊነት ለግል ፍላጎታችሁ ሳይሆን በህበርተሰባችን መካከል የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት እና ህዝባችሁን በታማኝነት ለማገልገል እንድትጠቀሙበት አደራ እላለሁ ብለዋል።

በያዝነው ዓመት የባሕል ፍርድ ቤቶችን በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች  እውቅና የመስጠት እና የማቋቋም ስራ ይሰራል ያሉት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው ፣ የባህል ፍርድ ቤቶቹን በማጠናከሩ ሂደት የቅድመ ስራ ሰልጣኝ ተመራቂዎቹ በሙሉ አቅም ማገዝ ይኖርባችኋል ብለዋል።

ምረቃችሁ የመጨረሻ ሳይሆን ህዝባችሁን ለማገልገል የምትነሱበት ምእራፍ ነው ያሉት ክቡር ፕሬዝዳንቱ፣ በሕግ የበላይነት የሚያምነውን እና  ያስተማራችሁን ማህበረሰብ አርአያነት ባለው ሙያዊ ስነምግባር እንድታገለግሉ አደራ እላለሁ ብለዋል።

በምረቃ ስነስርዓቱ  ላይ የተለያዩ መረሀግብሮች የተካሄዱ ሲሆን፣ በቆይታቸው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ የቅድመ ስራ ሰልጣኞች እውቅና እና ሽልማት ተሰጧቸዋል።