ASC Logo

አማራ ክልል 

ጠቅላይ ፍርድ ቤት

የፍርድ ቤት-መር የአለመግባባት መፍቻ ሥርዓቶችን መዘርጋት

የፍርድ ቤት-መር የአለመግባባት መፍቻ ሥርዓቶችን መዘርጋት
የፍርድ ቤት-መር የአለመግባባት መፍቻ ሥርዓቶችን መዘርጋት

በየትኛውም ጊዜ፣ አካባቢ እና ኅብረተሰብ እንደሚኖረው ሁሉ በአማራ ክልልም ሰዎች እና ቡድኖች በግላዊ፣ ቤተሰባዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ሲደርጉ አንዱ ከሌላው ጋር በሚያደረጋቸው መስተጋብሮችና ግንኙነቶች አለመግባባቶች እና ግጭቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ የክልሉ ኅብረተሰብም አለመግባባቶች እና ግጭቶች እንዳይከሰቱ የሚከላከልበት፣ የተፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመቆጣጠር ወይም ባሉበት ለመያዝ እና ለመፍታት የሚችልባቸው ልዩ ልዩ ባሕላዊ እና ዘመናዊ ሥርዓቶች አሉት፡፡ የክልሉ ፍርድ ቤቶችም ኅብረተሰቡ የተሟላ ፍትሕ እንዲያገኝ ዘመናዊ ፍርድ ቤቶች ከሚሰጡት መደበኛና የዘወትር የፍትሕ አገልግሎት በተጨማሪ በክልሉ ያሉ ልዩ ልዩ የባሕል ፍርድ ቤቶችን እና ሌሎች አማራጭ የአለመግባባት መፍቻ ዘዴዎችን በመደገፍና በማጠናከር ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ረገድ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከባሕል ፍርድ ቤቶች ጋር በተያያዘ እየተገበራቸው ካሉ በርካታ ተግባራት ሌላ እንደ ማግባባት/መደራደር (Negotiation)፣ አስማሚነት (Mediation)፣ ማስታረቅ (Conciliation) እና የግልግል ዳኝነት (Arbitration) የመሳሰሉ ዘመናዊ አማራጭ የአለመግባባት መፍቻ መንገዶችን ከፍርድ ቤቶች ጋር በማስተሳሰር ፍርድ ቤት-መር የአለመግባባት መፍቻ ሥርዓቶች (Court-connected or court-annexed ADR) እንዲዘረጉና የተቀናጀ የፍትሕ አሰጣጥ እንዲዳብር እየተጋ ይገኛል፡፡ በዚህም መሠረት ከፍርድ ቤት-መር የአለመግባባት መፍቻ ሥርዓቶች (Court-connected or court-annexed ADR) መካከል የፍርድ ቤት-መር አስማሚነትን (Court-connected or court-annexed mediation) የሚመለከት መመሪያ አውጥቶ በተወሰኑ የተመረጡ የክልሉ ፍርድ ቤቶች የሙከራ ትግበራ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ይህን ወደ ሙሉ ትግበራ ለማስገባት በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ የአስማሚነት አንድ አካል እንደመሆኑ መጠን ፍርድ ቤት-መር አስማሚነት በፍትሕ አስተዳደር በተለይም በፍትሐ ብሔር ፍትሕ አስተዳደር አለመግባባቶችንና ክርክሮችን በአጭር ጊዜ፣ ያለብዙ ውጣ ውረድ፣ እንግልትና ወጭ፣ በራስ ባለቤትነትና ወሳኝነት አነታራኪ ጉዳዮችንና ከዚሁ ጋር የሚገናኙ ነገሮችን በሰላም በመነጋገር፣ አንዱ የሌላኛውን ወገን ፍላጎት፣ ጥቅም፣ መብት፣ ሁኔታ፣ አረዳድ፣ አተያይና የመሳሰሉ ጉዳዮች በመረዳትና በማወቅ፣ ለክርክር ቁልፍ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ በገለልተኛ አስማሚ አሳላጭነትና ከአድሎና ወገንተኝነት የራቀ ድጋፍ አማካይነት ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያስችል ዘዴ ነው፡፡ በግል መጠበቅ የሚገባቸውን ምሥጥሮች ይዞ በማስቀረት፣ በክርክር ሂደት ሊከሰቱ የሚችሉ ተጓዳኝ የአእምሮና የሞራል ጉዳቶች በማስቀረት ሰላማዊና ዘላቂ መፍትሔን ለማምጣት እድል የሚከፍት ነው፡፡ የሚፈርስ ቤተሰብን የሚታደግ፣ በክርክር ሂደት በረጅም የክረክርና የማስረጃ አቀራረብ፣ በጊዚያዊ እግድ፣ በልዩ ልዩ ሕጋዊ የሆኑና በሰበብ-አስባብ ሊቀርቡና ሌላኛውን ወገን ለብስጭት፣ ለልዩ ልዩ ጉዳቶች በማጋለጥ የተበዳይነት ስሜትንና በቀል ማርገዝን የሚያስቀር ጤነኛ የሆነ ጉርብትናን፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነትን ለማስቀጠል የሚያስችል፣ የፍርድ ቤት የጉዳይ ክምችትን ከመቀነስና ክርክርን በወቅቱ ከመቋጨት ያለፈ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት የአለመግባባት መፍቻ መንገድ ነው፡፡