የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ሥልጣን እና ተግባር
በተሻሻለው
የአማራ ክልል ሕገ መንግስት እንዲሁም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግስት መሰረት የዳኝነት ስልጣን የተሰጠው ለፍርድ ቤቶች ብቻ ሲሆን
የዳኝነት ሥልጣኑም በፌደራል እና በክልሎች የተከፋፈለ ነው፡፡ በክልሉ ውስጥ የዳኝነት ሥልጣን እና ኃላፊነት ተግባራዊ የሚያደርጉ
በሶስት ደረጃዎች የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና ወረዳ ፍርድ ቤት ተቋቁመዋል፡፡ ፍርድ ቤቶች ማንኛውን በዳኝነት
ታይቶ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ አይተው የመወሰን ስልጣን የተሰጣቸው ሲሆን ህግ የመተርጎም እና የመተግበር፣ አለመገባባቶችን የመፍታት፣
በህግ የተረጋገጡ መብቶችን ማስከበር፣ በአስተዳደር አካላት የሚወጡ መመሪያዎችን እና ውሳኔዎችን መከለስ፣ ትዕዛዞችን እና ውሳኔዎችን
የመስጠት እንዲሁም በወንጀል ጉዳዮች ላይ ቅጣት መወሰን ስልጣን የተሰጣቸው ሲሆን የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ ሰብአዊ መብቶችን እና ነጻነቶችን ማስክበር፣
በእኩልነት ፍትሕ የማግኘት መብትን ማረጋገጥ እንዲሁም ሥልጣን የመቆጣጠር እና ሚዛን የማስጠበቅ ሚና አላቸው፡፡
በክልሉ
የሚገኙ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ስልጣን በተሻሻለው የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 281/2014 አንቀጽ 14 ላይ
በዝርዝር ተመላክቷል፡፡ የክልሉ ፍርድ ቤቶች በክልሉ የአስተዳደር ወሰን ውስጥ በሚወድቁ እና ቀጥሎ በተመለከቱት ጉዳዮች ላይ የዳኝነት
ስልጣን ተሰጥቷቸዋል፡-
·
የክልሉን ሕጎች መሰረት በማድረግ
በሚቀርቡ እና በፍርድ ሊወሰኑ በሚገባቸው ማናቸውም ዓይነት ጉዳዮች፤
·
በሌላ ሕግ በፌደራል ፍርድ
ቤቶች ወይም በሌሎች የዳኝነት ሥልጣን በተሰጣቸው አካላት እንዲታዩ ተለይተው ከተመለከቱ ጉዳዮች ውጭ በሆኑ ማናቸውም ጉዳዮች ላይ፤
·
በሌላ ሕግ በፌደራል ፍርድ
ቤቶች ወይም በሌሎች የዳኝነት ሥላጣን በተሰጣቸው አካላት እንዲታዩ ተለይተው ከተመለከቱ ባለጉዳዮች ውጭ በሆኑ ማናቸውም ሰዎች ላይ፤
·
በሌሎች ሕጎች ተለይተው ለክልል
ፍርድ ቤቶች በተሰጡ ማናቸውም በፍርድ ሊወሰኑ በሚገባቸው ጉዳዮች፣ ሰዎች እና ንብረቶች ላይ የዳኝነት ስልጣን የተሰጣቸው ሲሆን
የትኛውም የክልሉ ፍርድ ቤት በሥልጣኑ ሥር የሚወድቅ ጉዳይን በዳኝነት እየተመለከተ እያለ ወይም ፍርድ ከሰጠ በኃላ መደበኛ ኗሪነቱ
ከክልሉ ውጭ የሆነ ሰው በማንኛውም ሁኔታ ወደ ክርክሩ ቢገባ ወይም ከመድኅን ውል ጋር በተያያዘ መድኅን ሰጭው በክርክሩ ውስጥ ቢገባ
የፍርድ ቤቱን ስልጣን የሚቀይረው አይሆንም፡፡
የክልሉ ፍርድ ቤቶች ከላይ በተዘረዘሩት በክልሉ የአስተዳደር ወሰን ውስጥ ከሚወድቁ ጉዳዮች በተጨማሪ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የከፍተኛ ፍርድ ቤቶች በክልሉ የአስተዳደር ወሰን ውስጥ በሚወድቁ የፌደራል ጉዳዮች እና በፌደራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ሥልጣን ሥር የሚዳኙ ሰዎች ላይ የውክልና የዳኝነት ስልጣን አላቸው፡፡ በዚህም መሰረት፡-
· የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት
በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሥልጣን ሥር በሚወድቁ ጉዳዮች ወይም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ሥልጣን ሥር በሚዳኙ ሰዎች ላይ
የውክልና የዳኝነት ሥልጣን አለው፡፡
· የክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች
በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ሥልጣን ሥር በሚወድቁ ጉዳዮች ወይም በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች በሚዳኙ ሰዎች
ላይ የውክልና የዳኝነት ሥልጣን አላቸው፡፡
· እንዲሁም ከዚህ በተጨማሪ በሥነ-ሥርዓት
ሕጎች ወይም በሌሎች ሕጎች የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ ከክልሉ ጋር የሚያያዙ ወይም በክልሉ የአስተዳደር ወሰን ውስጥ የሚወድቁ
የግለሰብ አለም አቀፍ ሕግን የሚመለከቱ ጉዳዮችን እና የውጭ ሀገር ፍርድን፣ ውሳኔን፣ ብይን ወይም ትዕዛዝ ለማስፈጸም የሚቀርቡ
አቤቱታዎችን በውክልና የዳኝነት ስልጣን ይመለከታሉ፡፡
በሌሎች ሕጎች ለክልሉ
ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ስልጣን የተሰጠባቸውን ጉዳዮች ስንመለከት፡-
·
በአማራ ክልል የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር
292/2017 መሰረት የአስተዳደር መመሪያዎችና ውሳኔዎችን የመከለስ የዳኝነት ስልጣን፤
· በአሠሪ እና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 መሰረት
የሥራ ክርክር በሚመለከት የተከራካሪ ወገኖች ማንነት ላይ ሳይወሰን አከራክሮ ውሳኔ የመስጠት ስልጣን ለክልሉ ፍርድ ቤት የተሰጠ
ሲሆን፣ በክልሉ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 252/2009 እና የአማራ ክልል የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁጥር
79/1995 በተመሳሳይ ሁኔታ የገጠር እርሻ መሬት ላይ የሚነሳ ክርክር እንዲሁም ፍቺን በሚመለከት የሚቀርቡ ጉዳዮችን በተከራካሪ
ወገኖች ማንነት ላይ ሳይወሰን አከራክሮ ለመወሰን የዳኝነት ስልጣን ለክልሉ ፍርድ ቤቶች ተሰጥቷቸዋል፡፡